top of page

የልጁን መልክ መምሰል

 

 

 

 

 

“ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።

” (ኤፌ.4፥13)

መግቢያ

በዘመናችን ሰዎች ክርስቶስን በትክክል መሆን እንደሚቻላቸው አያሌ የስህተት ትምህርቶችን መስማት ከጀመርን ሰነባብተናል። አንዳንዴ ክርስቶስን የፍጥረቱ አካል በማድረግ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እኛ ራሱ ክርስቶስን ልንሆን እንደምንችል በአደባባይ ታውጆአል፤ በተለያየ መንገድ ይህን ትምህርት ፊት ለፊት በመቃወም፣ የትምህርቱን ስህተትነትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተቀዳ መሆኑን ቤተክርስቲያን ስታስተምርና ስትናገር ሰንብታለች አሁንም ታስተምራለች። ዛሬም ክርስቶስ የፍጥረት አካል እንዳይደለ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተማሩንን፣ ፍጹም አምላክነቱና ፍጹም ሰውነቱን  ደፍረን እንናገራለን ደፍረን እናስተምራለን።

   ትምህርቱን በምንቃወምበት ትይዩ ደግሞ እውነተኛውን ትምህርት ማስተማር ይገባናል፤ ስለዚህም፣ ከዚህ በኋላ “ወደ ክርስቶስ ማደግ” በሚል ርእስ፣ በተከታታይነት ወደ ክርስቶስ ከምን ተነስተን እንዴት ወደ ክርስቶስ እንደምናድግ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ያገኘነውን እናስተምራለን። በግልጥ ቃልም ወደ ክርስቶስ ማደግ ማለት፣ ክርስቶስ ራሱን አለመኾንና የእርሱ ገንዘብ መኾን እንደ ኾነ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ደፍረን እንመሰክራለን፤ እንናገራለን።

 

 

  አመጣጣችን ከየት ነው? 

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ እኛን በእርሱ መልክና አምሳል ፈጠረን (ዘፍ. 1፥26)። እግዚአብሔር ሰው በራሱ መልክና አምሳል መፍጠሩ በእኛ ላይ ትልቅ ዓላማ እንዳለው ማስተዋል ይቻላል፤ ከዚህም ባሻገር፣ እኛን የፈጠረበት ዓላማው ክብሩና ከሌላ ፍጥረት ልዩትነት ባለው መንገድ፣ ከእርሱ ጋር ቀጥታ ሕብረትን እንድናደርግ፣ እንድንነጋገርና ምላሽን በመስጠት እንመስለው ዘንድ ጽድቅን፣ ፍቅርን፣ ክብርን፣ ሞገስን፣ ዕውቀትን፣ ቅድስናን … ከፍሎ በመስጠት እንደ ኾነ ቅዱስ መጽሐፍ በሙላት ያስተምረናል፤ (ዘፍ. 3፥8፤ ኤፌ .4፥24፤ ቈላ. 3፥10)። ፍጹማንና ኃጢአት የሌለብን ቅዱሳን ስለ ነበርንም፣ በኹለንተናችን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ተጎናጽፈን በዕርቃን ሳንተፋፈር በአንድነት ታይተን፤ እንመላለስ ነበር፤ (ዘፍ. 2፥25)።

  ነገር ግን የገዛ መንገዳችንንና ፈቃዳችንን በመከተል፣ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ኀጢአትን ሠርተን ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላን፤ የሰይጣንን የአታላይነት ድምጽ በመስማታችን፣ በእግዚአብሔር ፊት የምንንጓደድበትን መልክና አምሳል፤ ግርማና ሞገስ፤ ጽድቅና ቅድስና፤ ዕውቀት ማስተዋል አጣን ወይም በእግዚአብሔር ፊት የማያቆም አዳፋ፣ ርኩስ፣ ጥዩፍ(አስጸያፊ)፣ ፍጹምነት የጐደለን ሆንን። እግዚአብሔርን የምንመስልበትን መልካችንን በገዛ እጃችን አሳደፍነው።

 ስለዚህም፥ “አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ” (ዘፍ. 5፥3) እንደሚል፣ እግዚአብሔር ፍጹም በሆነው በራሱ መልክና አምሳል የፈጠረው ሰው፤ ባለመታዘዙ ምክንያት በተበላሸውና ባደፈው በራሱ መልክ አዳም ወንድ ልጅን ወለደ ተባለ። ስለዚህም፣ “በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤” (ሮሜ. 5፥14)። በዚህ ብቻ ሳያበቃ፣ “አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤” ይላል (ሮሜ 3፥9) መላው ዓለም ከኀጢአት በታች የተገዛና የተከሰሰ ኾነ፡፡

  እንግዲህ እንዲህ የሆንነውን፣ እግዚአብሔር ያድነንና ወደ ልጁ መልክ እናድግ ወይም የልጁን መልክ እንመስል ዘንድ፣ እንደገና ጸጋ አበዛልን፤ አትረፈረፈልን፤ አሜን፡፡

እንዲህ ነበርን!

    አዳም “የመታዘዝን ፍሬ” ባለመብላት እንዲታዘዝ ቢነገረውም፣ እርሱ ግን የሰይጣንን ድምጽ ተከትሎ በመሄድና የተከለከለውን ወስዶ ከበላበት ቀን ጀምሮ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እርሱና ልጆቹ ሁሉ፣ እግዚአብሔር የተወን እየመሰለን አብዝተን ኃጢአትን ሠራን፤ ጨመርንም። ከዚህም የተነሣ፦

  1.  እጅግ ኀጢአተኞች ሆንን ነበርን “… ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ …” (1ቆሮ. 6፥9-11) እንደሚል ሁላችን ይህን ሁሉና ከዚህ ጋር ተመሳሳዩን ሁሉ ነበርን።

  የኀጢአተኝነት ዝንባሌ ከመጀመሪያው የተበላሸው፣ ሰው ከእግዚአብሔር በመለየቱና በእግዚአብሔር ላይ በማመጹ ምክንያት ነው። ስለዚህም እጅግ ባለመታዘዝ እጅግ ኀጢአተኞች ኾንን። በዚህም እግዚአብሔርን የምንመስልበትን መልክ አሳደፍን (ዘፍ. 5፥3)።

   2.  በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ሆንን ነበርን “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤” (ኤፌ. 2፥1)፤ የኀጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር መለየት፣ እርሱ መንፈሳዊ ሞት ነው። ስለዚህም በኀጢአት የሞተ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ማድረግ እጅግ ይሳነዋል።

   እኛ በኀጢአታችን ከእግዚአብሔር በመለየታችን እንኖር የነበረው፣ በሞት ጥላ ውስጥ ወይም በሙታን በተወረረ የሙታን መንደር ውስጥ ነው። ይህ በመንፈሳዊው እውነት በቅዱስ ሚዛን ላስተዋለው፣ እጅግ አስከፊና መራራ ሕይወት ነው። ፍጻሜው ደግሞ ከተጣሉት መላእክት ጋር በአብሮነት መጣል፤ መተው ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ነውና እንደ ቸርነቱ መጠን ደረሰልን፤ አሜን።

 

   3.  ያለ ክርስቶስም ሆንን ነበርን “በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።” (ኤፌ. 2፥12) በኤፌሶናውያን ላይ የወደቀው ወቀሳ እኛንም በቀጥታ ያገኘናል፤ ምክንያቱም በርግጥም እኛ መጀመሪያ ሕግንና ኪዳንን ከተቀበሉ ወገኖች መካከል አልነበርንም፤ የኪዳኑም ተካፋዮች አልነበርንም፤ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ እውነተኛውን አምላክ እግዚአብሔርን ባለማወቅ ያለ ክርስቶስ ነበርን።

   ያለ ክርስቶስ መሆን ከሕይወት መነቀል ነውና፣ ያለ ክርስቶስ ምንም፤ ባዶዎች ነበርን። ያለ ክርስቶስ በነበርንባቸው ዘመናት ሁሉ ያለ ተስፋ በባዶ ነበርን፤ ክርስቶስንም ባለማወቅ ጥልቅ ጨለማ ውስጥ ስንርመሰመስ ነበርን። ከዚህም ባሻገር እጅግ ርቀንም ነበርን (ኤፌ. 2፥13፤ 17)፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ፤ (መዝ. 103፣12)፤ አሜን።

    4.  ጨለማ የሆንን ነበርን “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤” (ኤፌ. 5፥8)። በአዲስ ኪዳን ምንባብ ውስጥ፣ “ጨለማ” ከብርሃን ተቃራኒ ከመሆን ባሻገር፣ ፍጹም ክፋትን ገላጭ ሃሳብ ነው። ሰው ኀጢአትን ባደረገ ጊዜ ብርሃንን የሚጠላ ሆነ፤ ጨለማን ደግሞ ወደደ፤ “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ … ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤” (ዮሐ. 3፥19-20) እንዲል ጨለማነት የፍጹም ክፋት መገለጫነት ነው፤ ስለዚህም ሁላችን እንዲህ ነበርን።

   ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው፤ በኀጢአት ጸንቶ የሚኖር ኹሉ የክርስቶስን ብርሃንነት በመቃወም በጨለማ ኀጢአት መኖርን የመረጠ ነው። በክርስቶስ የሚኖሩ ግን ከጨለማ በመውጣት በሚያስደንቅ ብርሃን ውስጥ ይመላለሳሉ፤ አሜን።

   

     5. በሃሳባችን ጠላቶች ነበርን ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት፣ “… ክፉ ሥራንም በማድረግ በሃሳባችን ጠላቶች ነበርን” (ቈላ.1፥21-22)፡፡ እጅግ ክፉዎች ከመሆናችን የተነሣ በእእምሮአችንና በልባችን ለራሳችን የምናዳላ ራስ ወዳዶች ነበርን፡፡ በምድር ላይ አንድም መልካም ሰው መገኘት እስከማይችል ድረስ ሁላችንም ለእግዚአብሔር ጠላቶች ነበርን፡፡

ዝንባሌአችንም አንዳች መልካም ነገርን ማመንጨት የማይችል ደካማና ክፉ ነበር፡፡ ሰይጣን እንደ አሻንጉሊት ሲጫወትብን እኛ ሁላችን በሃሳባችን የሰይጣንን ፈቃድ እንፈጽም ዘንድ ባሮችና ለእግዚአብሔር ከቶውንም የማንመች ጠላቶች ነበርን፡፡ ጳውሎስ ይህን በብዙ መንገድ አስፍቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “ገና ደካሞች ሳለን … ገና ኃጢአተኞች ሳለን … ጠላቶች ሳለን” (ሮሜ 5፥6፡ 8፡ 10) በማለት በክፋት እንዴት ጸንተን እንደ ነበርን አስረግጦ ይናገራል።

    6. ወገን፤ ምሕረትም ያገኘን አልነበርንም “እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም … እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም” (1ጴጥ. 2፥10) እንኪያስ ምን ነበርን? ብለን ብንጠይቅ፣ “ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።” እንዲሁም፣ “አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ ነበርን” (ኤፌ. 2፥3፡ 11)፡፡ ከዚህም የተነሣ ከእግዚአብሔር ዘንድ በኀጢአታችን ምክንያት እጅግ ርቀን ነበርን፡፡

   ከኪዳኑ ያፈነግጥን፣ ባለመታዘዝ የጸናን፣ የገዛ መንገዳችንን ተከትለን እንደ በጐች የተቅበዘበዝን፣ ያገኘን ጠላት ሁሉ የነዳን፣ ለተገዛንለትም ሁሉ ባሮች ሆነን እጅግ ምስኪኖች የነበርን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከትልቅ ፍቅርና ምሕረቱ የተነሣ ሁላችንን ያድነን ዘንድ እንዲሁ ወደደ፤ ፈቀደም፡፡አሜን

ይህን ስንል በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር የሚያድንና የሚታደግ አምላክ ሆኖ አልተገለጠም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንም የኪዳኑን ሕዝብ በብዙ ታድጐ ጠብቋል (ዘዳግ. 26፥8፤ መዝ. 27፥1፤ 88፥1) ፤ ነገር ግን ፍጹም የሆነውን መዳን በሰው ልጅ ያደረገው በክርስቶስ ኢየሱስ ላመኑትና ለተቀበሉት ሁሉ ነው።

 

በእርግጥም ምንም እንኳ ይህን ሁሉ የነበርን፤ በድቅድቅ ጨለማ እንደሚኖር ሰው ፈጽሞ ከየት ወደየት እንደምንሄድ ሳናውቅ በብዙ ጥፋት ስንኖር የነበርን ብንሆንም በምሕረቱ ባዕለጠጋ የሆነው ጌታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ያመንነውን ልጆቹን፦ 

 

    ያደረገን እንዲህ ነው፦

   1.      ክርስቶስ ኢየሱስ የሞትን ኃይል አስወግዶ የሕይወት ኃይል ሰጠን ፤ አጠበን ፤ ቀደሰን ፤ አጸደቀንም (1ቆሮ. 6፥9)።

ይህን ልብን የሚመላ፤ አዕምሮን የሚያልፍ ድንቅ ነገር ነው! ይህንን ጽድቅ፤ ቅድስናና ንጽሕና የምናገኘነው ወይም የሚሰጠን በክርስቶስ ኢየሱስ (ሮሜ.3፥24) ሲሆን፥ ይኸውም በሞቱና (ሮሜ 3፥25፤ 5፥8) በትንሣኤው (ሮሜ 5፥10) እንዲሁም ዘወትር ትኩስ ሆኖ ዛሬም ድረስ በሚታይልን (ዕብ.9፥24)፥ ከአቤል ደም ይልቅ የተሸለውን በሚናገርልን (ዕብ. 12፥24) በደሙ ኃይል ነው።

    2.      በጌታ ብርሃን ሆንን፦ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ”፤ “አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ (ማቴ. 5፥14 ፤ ኤፌ. 5፥8)

ብርሃኑ በሕይዋተችን ብቻ ያበራ አይደለም ፤ ጨለማ ለወረሰው ለአሮጌው ሰው ጠባይ ሁሉ የምንታይና በዝምታ የምንወቅስ በማድረግ ነው፤ ብርሃን እንድንሆን የወደደው (ማቴ. 5፥14) ብርሃኑ በእርሱ ዘንድ ያለማንነት እንጂ ከእኛ የሚመነጭ አይደለም። ብርሃኑ ከእርሱ ለእኛ የሆነልን ስለሆነ ክብሩና ውዳሴው ለእርሱ  ብቻ ነው። “የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል” (ራእ. 5፥12) እንዲል።

    3.      በክርስቶስ ደም የቀረብን ሆንን (ኤፌ. 2፥13)፦

የገዛ መንገዳችንን ተከትለን ከክርስቶስ ብንርቅ፤ ራሱ ክርስቶስ በደሙ ቀረበን፤ አቀረበንም። ይኸውም “እንደእግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኃጢአት ይቅርታ” ባገኘንበት ሞቱ ነው (ኤፌ. 1፥7) በመከራውና በሞቱ የፈሰሰው ደም ለኃጢአተኞች ሁሉ የተከፈለ ውድ ዋጋ ሆኖ ማንም ወደማይቀርበው ወደ እግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ በኩል ለመቅረብ በቃን።

ከክርስቶስ የራቅን ሁላችን መቅረቢያችን ራሱ ክርስቶስ ብቻ ነው። መራቅ የቀደመ ሥፍራን ሙሉ ለሙሉ መልቀቅን ያመላክታል። በእግዚአብሔር ገነት የነበረንን ሥፍራ በሰይጣን ምክር ተታልለን ፤ በገዛ ፈቃዳችን ትተን ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልለን ወጣን፤ ራቅንም (ዘፍ. 3፥8፤ 24) በክርስቶስ ቀረብን ስንል ያንን በእግዚአብሔር መልክ ልንኖርበት የሚገባውንና የሚልቀውን ክብርና ሞገስ በእርሱ ክብርን ሁሉ ወርሰን ቀርበናል ማለታችን ነው።

    4.      ያለ ክርስቶስ የነበርነውን ሁላችን በእርሱ በክርስቶስ፤ ለክርስቶስ ሆንን

አባት የሚወደው ልጅ ከባድ ወንጀል ቢሠራበት፤ ስለልጁ ፈንታ ጥፋቱን አምኖ በመቀጣትና በመካስ ልጁን ነጻ በማውጣት ገንዘቡ እንደሚያደርገው፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔርን ድምጽ ከመስማት ርቆ በመሄድ የበደለውን የእኛን ማንነት ራሱ አምኖ ስለእኛ ኃጢአት የሌለበትን ኃጢአተኛ በማድረግ (2ቆሮ. 5፥21) ስለ እኛ መርገም ሆኖልን (ገላ. 3፥13) ተቀጥቶ፤ ክሶ፤ ተቤዥቶ ነጻ በማውጣት ያለክርስቶስ የነበርነው በክርስቶስ ለክርስቶስ አደረገን። ከሕግ  እርግማንም ዋጀን።

 

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ ?

 

እግዚአብሔር ሃይማኖታዊ ዝንባሌና መልኩ ብቻ እንዲኖረን አይወድም። “ሙሉ ሰው ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ” ለማደግ፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት መምጣት (ኤፌ. 4፥13)፤ ስለ እውነት ስለ እግዚአብሔር ልጅ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል።

   ስለ እውነትና ስለ እግዚአብሔር ልጅ ለማወቅ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ተጠቅሰዋል። አንድነትና ማደግ።

              አንድነት፦

ክርስቶስን በማመን ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ አንድነትን ያሳያል።

  “እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።” (ኤፌ.4፥1-6)

  ይህም ያመኑትን አማኞች የሚያመለከት ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት። እርሱ ደግሞ ራሷ። በቤተ ክርስቲያን ላይ ዋና ብቸኛ ሥልጣን ያለው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው።

    የቤተ ክርስቲያን አንድነት የተገኘው ጌታ አብ በልጁ  ክርስቶስ እንዳይበላሽ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ክርስቲያኖች ሁሉ ይህ አንድነት ቤተ ክርስቲያን ይህን አንድነት “በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ” (ሐዋ. 2፥42) እንደ ነበረው፥ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ሞቱን፣ መቀበሩንና ትንሣኤውን፥ በዚህም የተገኘውን የኃጢአት ሥርየትና መዳንን የሚያውጀውን ጌታ ያስተማረውን የሐዋርያትን ትምህርት በማጥናት አንድ ሊሆኑ ይገባቸዋል።

   አንድነት የበጉ መንግሥት ዋና መገለጫ ነው፤ (ራእ. 20፥4) በዚህች ምድር ያለችም ቤተ ክርስቲያን [ክርስቲያኖች] አንድነት ዋና ነገሯ መሆኗን መዘንጋት የለባትም። በአንድነቱ ውስጥ የሚሰጡት ልዩ ልዩ ጸጋዎችም “የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ” (ኤፌ. 4፥12 ዓ.መ.ት) ነው እንጂ ለግል ጥቅም ወይም በአንድነቱ ውስጥ ምዕመናን ሥራቸውን ራሳቸው እንዲሠሩ የሚያዘጋጇቸው ናቸው። ቤተ ክርስቲያን እንድናገለግልበት የተሰጠንን ጸጋ ለግል ጥቅም ማዋል አስነዋሪና ኃጢአት ነው፤ ሰጪው በመጣ ጊዜ በፍርድ ይቀበለናል።

     ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያንን ሁሉ መከራ ከፍሏል። የግል ሕይወትን አብልጠን የክርስቶስን አንድነትና የቤተ ክርስቲያን አካል ቸል ብንል ተግሳጹ ያገኘናል።

   

         ማደግ፦

የምናድገው “በክርስቶስ ወዳላው ፍጹምነት” ነው። ስናድግም ከአንድነቱ ሳንነጠል በዚያው ውስጥ እያለን ነው። በግል የምናድገው  የራሳችን ዕድገት የለንም። የተሰጠንን መንፈሳዊ ጸጋ ሙሉ ለሙሉ ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለራሳችን ማዋል እንደሌለብን አንስተናል። አካሉ ወደፍጹም ሙላት፤ ሕንጻው ወደፍጹምነት እንዲያድግ ከተፈለገ እያንዳንዱ ብልት ወይም የሕንጻው ክፍል ራሱን እንዲችል መሥራት ይገባል።

  አገልጋዮች ምዕናንንን ወደ ክርስቶስ መሳብና ማሳደግ አለባቸው እንጂ ሁል ጊዜ በሞግዚትነት ሊመሯቸውና ሊጠብቋቸው አይገባም። የተጠናቀቀ ሕንጻ አገልግሎት ራሱን ችሎ እንደሚሰጥ፣ ሁሌም ሲታነጽ  እንደማይኖር ሁሉ፣ ሁል ጊዜ እየተሠራን በሚያኖር ማንነት መኖር የለብንም። ሁሉ ጊዜ ቃሉን የምናስጠናቸው፤ መልሶቻቸውን የምንመልስላቸው፤ ያለእኛ ሙሉ እንዳልሆኑ እንዲያስቡ ከማድረግ ልንከለክል ይገባል።

     በራሳቸው የሐሰትና የእውነት መምህራንን ትምህርት መመርመር የሚችሉበትን ጥበብ ልናሳያቸው፤ ወደቤርያዊ ልበ ሰፊነት(ሐዋ. 18፥10) እንዲደርሱ መንገድን ማሳየት አለብን። የሰውነታችን አካላት ሁሉም እኩል እንዲያድጉ፤ አንዱ ግን አስተዳደጉ ቢያስተጓጉል፣ ብዙ ነገር እንደሚያስተጓጉለው የክርስቶስ አካላት የሆኑትም ምዕመናንም ሁሉ ከጸጋ ሳይጐድሉ ፍጹም በእኩልነት ሊያድጉ የሚችሉባቸውን መልካምና የተመሰከረለትን ሥራ ልንሠራ ይገባናል።

     በክርስትና ትምህርት ዕውቀት ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የሚገልጠውን የግል ብስለት ሳይሆን ፍጹም ሚዛናዊ በሆነው በክርስቶስ ባሕርይን ማደግን ያሳያል። ይህም በዓላማ አንድ መሆንንም ጭምር የሚያሳይ ነው። ጌታ ኢየሱስ የሁሉንም አካላቱን ጤንነቱን እጅግ ይፈልጋቸዋል። የእኛ ብርታት ብቻውን አይቆምም፤ ዓይን ጤናማ ቢሆንም ደኅንነቱ በሌሎች ብልቶች ላይ ይመሠረታል። የአንዱ ክርስቲያን ሕብረት ድካምና ውድቀትም የሌላውን ክርስቲያን ሕብረት ማስነቀፉና ማዋረዱ አይቀርም። ስለዚህም ወደ ክርስቶስ ስናድግ የተከፈለልንን እናስተውል፥ እርሱን “የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን  በመመልከት” (ዕብ. 3፥1) ሕንጻው እየተጋጠመ ውብ ቤት እንደሚሆንና እንደሚሠራ ሁላችን ለክርስቶስ ቤትነት የተገባን ቤት ሆነን እንሠራ ዘንድ ወደ ክርስቶስ ተያይዘን ልናድግ፤ ልንተናነጽ ይገባናል።

ካሱ ቦስተን

መሪና ተባባሪ

 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ የመሪና የተባባሪ ድርሻን ከሚገልጡ ታሪኮች አንዱ የሙሴና፣ የአሮንና የሖር ታሪክ ነው(ዘጸ. 17÷8-16)፡፡

 

    አማሌቃውያን ከእስራኤል ጋር ሲዋጉ ኢያሱ ጎልማሶቹን ይዞ ከአማሌቃውያን ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ ሙሴ ደግሞ ወደ ኮረብታው ወጣ፡፡ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርጋሉ፡፡ ሙሴ ደክሞት እጁን ባወረደ ጊዜ ደግሞ አማሌቅ ድል ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሙሴ ቀኑን ሙሉ ዋለ፡፡ በመጨረሻ ግን የሙሴ እጆች ከበዱ(ደከሙ)፡፡ ይህን የተመለከቱት አሮንና ሖር ለሙሴ የድንጋይ ወንበር አዘጋጁለት፤ ሙሴም እዚያ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እጁን ዘረጋ፡፡ ድሉም ለእስራኤል ሆነ፡፡ ነገር ግን አሁንም ሙሴ እጆቹ እየደከሙ መጡ፡፡ አሮንና ሖርም በግራና በቀኝ ሆነው የሙሴን እጆች ከፍ አድርገው ደገፏቸው፡፡ ያን ጊዜ ሙሴ እጆቹን አነሣ፡፡ እስራኤልም አማሌቅን ፈጽመው ድል አደረጉ፡፡

 

    አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆው ብቻውን አይደለም፡፡ እንኳንና በሰዎች የተመረጠ መሪ እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ እንኳን ብቻውን ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ መሪ ምን ጠቢብ፣ ጎበዝ፣ ውጤታማ፣ ተወዳጅና ዐቅም ያለው ቢሆንም እንኳን እንደ ሙሴ እጆች መዛሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ አሮንና እንደ ሖር መንገዱን አይቶ የሚደግፈው ይፈልጋል፡፡ መልካም መሪ ውሳኔዎቹ፣ የለውጥ ሐሳቦቹ፣ ዕቅዶቹና ቃል ኪዳኖቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያበረቱት እንደ አሮንና ሖር የመሳሰሉ አጋዦች ያስፈልጉታል፡፡ አሮንና ሖር ለሙሴ የተሰጠው ሃላፊነት ወይም ራዕይ አልተሰጣቸውም፡፡ ነገር ግን ሙሴን ደግፈው የሚፈልጉትን ውጤት አመጡ፡፡ ሁሉም ሰው መሪ ባይሆንም የመልካም መሪን ሐሳብ፣ ዕቅድ፣ ራእይና ውሳኔ በመደገፍ ግን ለውጥ ማምጣት ይችላል፡፡

 

    ሙሴ አንድ ሲሆን ደጋፊዎቹ ግን ሁለት ነበሩ፡፡ ምንጊዜም ከደጋፊዎች ተደጋፊዎች ያንሳሉ፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለምን የለወጧት ጥቂት ባለ ተሰጥዖዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸውን፣ መንገዳቸውን፣ አመራራቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ጥረታቸውን የሚደግፉ አካላቶች ነበሯቸው፡፡  በቤተክርስቲያንም መርሁ አንድ ነው የቤተክርስቲያን መሪዎች እንዲሁም የየአገልግሎት ክፍል መሪዎች ሊደገፉ አይዞአችሁ ሊባሉ ከጎናችሁ ነን ሊባሉ ይገባቸዋል፡፡ መሪዎች ወይም ቤተክርስቲያንን ወደታየላት ግብ ለማድረስ ራዕይ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ባለራዕዮች ስኬታማ የሚሆኑት የአገልግሎት ክፍሎች፣ በተለያየ ጸጋ የሚያገለግሉ አገልጋዮች፣ እንዲሁም ምዕመናን፣ ማግኘታቸው መሆኑን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡

 

     ብዙ ሙሴዎች እንደ አሮንና ሖርን የመሰሉ አጋዦች አጥተው እጃቸው ዝሎ ድል ሆነዋል፡፡ መንገዱ፣ ሐሳቡ፣ ውጣ ውረዱ፣ ሙግቱ፣ ጭቅጭቁ፣ የሰው ትችትና ወቀሳ፣ ስድብና ዕንቅፋትነት አዝሏቸው ድል ከማድረግ ድል ወደመሆን ወርደዋል፡፡ በህይወት ዘመናችን ብዙ ሙሴዎች ተሰጥተውን ነበር፡፡ነገር ግን የሚያግዛቸውና ክንዶቻቸውን የሚደግፍ፤ ቢያንስ የድንጋይ መቀመጫ እንኳ የሚሰጥ አጥተው በሞትና በሽፈት ድል እየሆኑ ተገቢውን ለውጥ ሳያመጡ ቀርተዋል፡፡ ኧረ እንደውም ድንጋዩን እንዲቀመጡበት ከማድረግ ይልቅ ድንጋዩን እየወረወርን የፈነከትናቸው ስንቶች ይሆኑ?

 

      ድል የማድረጊያ አንዱ መንገድ ብርቱዎቹን መደገፍ ነው፤ ክንዳቸው፣ ድምጻቸው፣ ሥራቸው፣ ጥረታቸው፣ ሐሳባቸው፣ ራዕያቸው ከፍ ሲል ድል እንዲያደርጉ መደገፍ ነው፡፡ መጥፎ ሠሪዎችን የምንቃወመውን ያህል መልካም ሠሪዎችን የማንደግፍ ከሆነ ውጤት አናመጣም፡፡

 

የሙሴም ታላቅነት ምን መሪ ቢሆን፣ እጆቹ ታላቅ ሥራ የሚሠሩና ድል አድራጊ ቢሆንም ሊደክም፣ ሊሸነፍ፣ ሊያቅተውና ሊዝል እንደሚችል አመነ፡፡ ያለ ሌሎች ድጋፍ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ተቀበለ፡፡ ታላቅነት ማለት የታናናሾችን አስተዋጽዖ መናቅ አይደለም፡፡ ሁሉን ብቻዬን አደርገዋለሁ አላለም፡፡ አሮንና ሖር እንደሚያስፈልጉት ተቀበለ፡፡ ጎበዝ ሰው እንዲህ ነው፡፡ ሁሉንም ለብቻዬ እችለዋለሁ አይልም፡፡ የአንድ ሰው ውጤታማነት የብዙ ሰዎች አስተዋጽዖ ውጤት ነውና፡፡ ድል የሙሴም፣ የአሮንና የሖርም የየብቻ ውጤት አይደለም፡፡ ድል የሙሴ፣ የአሮንና የሖር የኅብረት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ በፍቅር በህብረት ለድል እጅ ለእጅ እንያያዝ አሜን፡፡ በሌላ ጽሁፍ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት ተባረኩ ለበረከትም ሁኑ ፡፡

ካሱ ቦስተን

    የፋሲካ በዓል

" ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው በዚያ ስፍራ ከግብፅ በወጣህበት ወራት፥ ፀሐይ ሲገባ፥ ማታ ፋሲካን ሠዋ።" ዘዳግም 16:6

ፋሲካ እስራዔላውያን ከግብጽ ምድር ከመውጣታቸው በፊት ያከበሩት በዓል ነበር ። በዘጸዓት 12 ላይ እንደምናነበው የእስራኤል ልጆች ፋሲካን ያዘጋጁት በዚያች ለሊት የግብጽን በኩር እንዲገድል ከተላከው ለመዳን ነበር ።

" ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም።" ዘጸዓት 12:13

እንግዲህ ፍሲካ በመጀመሪያ ደረጃ ከእግዚአብሔር ፍርድ የዳኑበት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ሊያጠፋ ከመጣው አጥፊ የዳኑበት ነበር ።

 

" እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም። " ዘጸዓት 12:23

ፋሲካ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምሳሌ ነው። ከሁሉም የሚቀድመው ከእግዚአብሔር ጋር ለሚኖረን አንድነት መሰረቱ በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከእግዚአብሔር ቁጣ መዳኑ ነው። እግዚአብሔር ልጁን የላከው ስለዚህ ነውና። ዮሐንስ ኢየሱስን ተመልክቶ " እነሆ የግዚአብሔር በግ ያለው ሃዋርያው ጳውሎስ ደግሞ " ... ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና የሚለው ለዚህ ነው።

ቃሉ እንደሚመሰክረው ያለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም ከሐጢአት ፍርድ የሚያድን ምንም ነገር የለም ። " መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።" የእስራኤል ልጆች መቃኑንና ጉበኑን ደም በመቀባት ከሞት ፍርድና ከፈርዖን የጭቆና ግዛት ነጻ እንደወጡ ሁሉ ዛሬም በክርስቶስ ደም ለምናምን የሃጢዓት ስርየትና መንጻትን፥ ቤዛነትን፥ ጽድቅን፥ ሰላምን እና አሸናፊዎች የመሆንን ስልጣንን አስገኝቶልናል። ደሙ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለውን ቃል ኪዳን አጽንቶልናል።

እንግዲህ ፋሲካ ከፍርድ መዳኛ ብቻ ሳይሆን የደህንነታችንና ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ሕብረትም መሰረት ለሆነው ምሳሌ ነው ። ፋሲካ ከሁሉ በዓላቶች ሁሉ ቅድሚያ ይሰጠዋል ። ምክኒያቱም ያለፋሲካ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ሊኖረን ስለማይችል ነው ። እስራኤላውያን ፍሲካን ያከበሩት ከግብጽ ሲወጡ ብቻ ሳይሆን በምድረ በዳ ጉዞ ላይና ወደተስፋይቱ ምድር ከገቡም በኋላም ነበር። ከግብጽ ባርነት ለመውጣት በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ የተረጨውን የበግ ደም ምሳሌ በማደሪያው ድንኳንም ሆነ በቤተ መቅደስ እስከመጨረሻ አላቆሙም።

"እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም።" ዕብ 9:22

ዛሬም ቢሆን እስከመጨረሻው ድረስ ተስፋችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው። አሜን ።

                       ካሱ ቦስተን 

                ----------------------------------------////-----------------------------------------

       

 

 

 

የጠፋው ልጅ   (ሉቃ.15፥28)

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ጠፍቶ ስለመገኘት ሉቃስ ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጠናል፡፡“ጠፍቶ የተገኘው” ህጻኑ ኢየሱስ(ሉቃ.2፥46)፣ ጠፍቶ የተገኘው በግና ድሪም (ሉቃ.15፥3-11) ሉቃስ የዘገባቸው እውነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡በእርግጥ በኃጢአት ጠፍቶ ለበጎነት እንደመገኘት ያለ ፍጹም ሰማያዊ ደስታ የለም፡፡(ሉቃ.15፥10)

     የጠፋው ልጅ የአባቱን ሀብት ለመካፈል ሲነሳ ወደአባቱ ቤት ለመመለስ ፈጽሞ ያሰበ አይመስልም፡፡ከአባቱ ቁጥጥር ውጪ በመሆን ያሻውንና የወደደውን ሊያደርግ በመፈለግ ወጥቶ የሄደ ነው፡፡“ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ የሄደው ወደሩቅ ሀገር ነው፡፡”(ሉቃ.15፥13) በሄደበት ሀገር ግን ሀብቱን በተነ፡፡ እንዳይመለስም እጅግ ርቆ ሄደ፡፡ የኃጥዕ መንገድ ከእግዚአብሔር የተለየ ነውና ሩቅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተለየው አዳም መልካም በሚመስለው መንገድ ሲጓዝ ፤በገነት እያለ ከእግዚአብሔር ሩቅ ነበር፡፡(ዘፍ.3፥6) በተመሳሳይ መንገድ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ወደተርሴስ የሄደው ዋጋ ከፍሎ፤ከስሮ ፤ርቆም ነው፡፡(ዮና.1፥3)

     የጠፋው ልጅ ከመራቁ ባሻገር በረሃብ ምክንያት የሚጨነቅም ሆነ፡፡ የረሃቡን ጭንቀት ለማስታገስ “ … ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።”(ሉቃ.15፥15) ይላል፡፡ የጠፋው ልጅ የእሪያ እረኛ በመሆን ያደረገው ይህ ድርጊት በአይሁድ ልማድና  በኦሪት ህግ እጅግ ርኩሰት ነው፡፡(ዘሌ.11፥7) ይህ ብቻ አይደለም ለእንሰሳት የሚሰጠውን የእህል ገለባ (አሰር) ሊበላ እየተመኘ እንኳ ሊያገኝ ያልቻለ ነበር፡፡

     ኃጢአተኝነት ያወረደው ማንነት የኢየሱስ ትንሳኤ ካላገኘው ከእንሰሳ እንኳ የሚያንስበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ከባህርይ ውጪ የእንሰሳ ምግብን መመኘት እጅግ ይከብዳል፡፡ በእርግጥ ይህ የጠፋ ልጅ በጣም ያሳዝናል፡፡ የዚህ ልጅ መጥፋት እውነተኛው ስብራትና ህመም የሚሰማው ለወለደው አባቱ ነው፡፡ ምንም እንኳ አባቱ ነጻነቱን የጠበቀለት ቢሆንም ልጁ በተቅበዘበዘና በባዘነ ጊዜ ፍጹም የማዳን እጅን ዘርግቶለታል፡፡ ወላጅ አባት ስለልጁ ስብራት ማንም አያስረዳውም፡፡ የልጁን ነገር ያለቋንቋም ይገባዋልና፡፡

     ልጁ የጠፋበት አባት ዓይኖች ደጅ ደጅ ብቻ የሚያዩ አይደሉም፤ይልቁን መንፈሱ ይቅበዘበዛል እንጂ፡፡ የጠፋው ልጅ በሆነው ሁሉ ወደልቡ ተመለሰ፤አዘነ፤ተጸጸተ፤ተነስቶም ወደአባቱ በመሄድ “አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።”(ሉቃ.15፥18) በማለት ለራሱ ተናዘዘ፡፡ እውነተኛ ንስሐ ለራስ ከመናዘዝ ይጀምራል፡፡በራሱ ፈርዶ፤ጥፋተኝነቱን አምኖ መጥቷልና አባቱ በምንም ነገር ሊወቅሰው አልወደደም፡፡ጌታም ለእኛ ያለው ሀሳብ ይህ ነው፡፡ራሳችንን በንስሐ ወቅሰን በመጣን ጊዜ የፍቅርና የሥርየት ደሙ ለይቅርታ እንጂ የቁጣውና የትዝብቱ በትር አያገኘንም፡፡

     ስለተገኘው ልጅ ሙሉ ደስታ ሆነ፡፡ ተካፍሎ ከሄደው ሀብት ይልቅ አሁን በመመለሱ ያገኘው ተቀባይነትና ማዕረግ ፤የልጅነት ሥልጣኑም በለጠ፡፡ አባቱ ከበደል የተመለሰ ልጁን ሲያገኘው ከሞትና ከመጥፋት ህያው ሆኖ ስላገኘው ልዩ በዓል፤ትልቅ ግብዣ አደረገለት፡፡ አብ የጠፋን ልጆቹን በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሞት ባገኘን ጊዜ ዘላለማዊ ደስታና በዓል በእግዚአብሔር ገነት ሆኖዐል፡፡

   በጣም የሚገርመው ደግሞ

      የጠፋው ልጅ በመገኘቱ፤ በተደረገው ደስታና በዓል በቤት የነበረው ታላቁ ልጅ ፍጹም ደስተኛ አልነበረም፡፡ “ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው።እርሱ ግን መልሶ አባቱን። እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው።”(ሉቃ.15፥28-30)

    አይሁድ በቤተ ክርስቲያን መመስረት ደስተኞች አልነበሩም፡፡ የቀደሙት “ታላላቅ” የኋለኞቹ ታናናሾች በመምጣታቸው ፈጽሞ አልተደሰቱም ፤ይልቁን አብዝተው ተቆጡ እንጂ፡፡ ይህ ወንድም የተቆጣ ብቻ አይደለም ታናሽ ወንድሙን “ይህ ልጅህ… ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር የበላ” በማለት እንደወንድም በማያይ ጥላቻና በንቀትም የተናገረ ነው፡፡በእርግጥ ግን ሰው ሲመለስ ለምን ይሆን ብዙዎች እንዲህ የሚንጨረጨሩት? የጌታ መንግስት እኮ እንዲህ ያሉ ደካሞችና ኃጢአተኛ ሰዎች የሚጋፏትና የሚናጠቋት ናት?(ማቴ.11፥12) ዛሬም ይህ እውነት ፍንትው ብሎ አለ፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት በአገልግሎት የቀደሙትና በቤቱ ያሉቱ ሌሎች “ኋለኞች” ከአለምና ከጠፉበት ሲመጡ ብዙዎቹ ደስተኞች አይደሉም፡፡ በሰውና በእግዚአብሄር ዘንድ አሳፋሪና አስነዋሪ ከሆኑት በደሎች አንዱ የደከሙት ሲመለሱና ፊታቸውን ወደጌታ ዘወር ሲያደርጉ የሚወርፉና የሚሳደቡ የስድብ አፎች መብዛታቸው ነው፡፡

     ለምን እንደሚቆጡና እንደሚሳደቡ ሳስብ “እገረማለሁ!”፡፡ ቁጣቸውና ስድባቸው ደግሞ ከሩቅ ይሰማል፡፡ አባቱ ስለጠፋው ልጁ በዓል ሲያደርግ፤ታላቅ ወንድም መርዶ ይቀመጣል፡፡ ዘማውያን ፣ዘፋኞች ፣ዓለማውያንና አህዛብ በፍጹም ንስሐ ተመልሰው አንዱን ጌታ ብቻ መርጠው ተገልግለው ሊያገለግሉ ሲመጡ ጥቂት ያይደሉ የቤቱ “ቀደምት ነዋሪ ወንድሞች አገልጋይ ነን ባዮች ከኛ ሌላ ላሳር ባዮች ” ግን ጠፍተው የተገኙ ወገኖችን የቀደመ (የበፊት በእግዚአብሄር ዘንድ የተረሳ የተደመሰሰውን ኃጢአት) ነውር ያጠናሉ፤ያጠነጥናሉ፡፡ ስለዚህም አብዝተው ይቆጣሉ፡፡ “እኛ ከጥንት እዚህ ነበርን ፤እኒህ ከወዴት መጡ?” የሚል የቀኝ አይን ቅላት ጥያቄ ያሠማሉ፡፡ እግዚአብሔር በልጁ ደም አጥቦ የረሳውን ኃጢአት አስታውሶ እንደመቆጣትና የክስ ምክንያት እንደማድረግ ከባድ ነውርና ኃጢአት ፈጽሞ የለም፡፡

     እናንተ ታላላቅ የቤቱ ቀደምት አገልጋዮች! እንደእኔ ያለ ፍጹም ኃጢአተኛና ነውረኛ ከጠፋበት በመጣ ጊዜ ስለምን ትቆጣላችሁ? እኔ የአባታችሁ ልጅ ወንድማችሁ ነኝና ከጠፋሁበት በመገኘቴ ደስ ይበላችሁ እንጂ በአንዳች አትከፉ፤አባቴም እንዲህ ይላችኋልና፦

       “ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል፡፡”(ሉቃ.15፥31-32)

                    አሜን፡፡ እንዲህ ይሁንልን፡፡                   

    ካሳሁን

 

_________________________ ////// ________________________

 

 

 

 

 

 

 


         

             እጅግ ወዳለችና ብዙ ኃጢያቷ ተሰርዮላታል 

አንድ ቀን ከፈሪሳውያን አንዱ ኢየሱስን በቤቱ ምሳ እንዲበላ ለመነውና ወደ ቤቱ ገባ። «እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።» (ሉቃ.7፡37-38) በዚህን ጊዜ ይህ ፈሪሳዊ በልቡ «ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።» በማለት አሰበ። ኢየሱስም የልቡን ሐሳብ አወቀና እንዲህ ሲል በምሳሌ አስረዳው «ኢየሱስም መልሶ፦ ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ። ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? ስምዖንም መልሶ፦ ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም፦ በእውነት ፈረድህ አለው።ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። እርስዋንም። ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት። (ሉቃ.7፡40-48)
          በዚህ አስደናቂ ታሪክ ውስጥ ወደ ኢየሱስ የምንቀርብበት አቀራረብ ምን እንደሚመስል። የሰው ሐሳብና የእግዚአብሔር ሐሳብ ምን ያህል የተራራቀ እንደሆነ። አሁንም በዚህች ቅጽበት ወደ ጌታ እየቀረብንበት ያለውን መንገድ እንድንፈትሽ ለማየት እንችላለን።
ለመሆኑ በዚህ ስፍራ ካሉት ሁለት ኢየሱስን ተቀባዮች የትኛውን ትመስላለህ? ትመስያለሽ? ይህንን ጥያቄ ለመሆን የምንፈልገውን ከማሰብ አንጻር ሳይሆን አሁን ጌታን እያስተናገድንበት ካለው እውነተኛ ገጽታ አንጻር ብንመልሰው የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን። መልሳችን መሆን ያለበት በውድድር እንዳለ ሰው ነጥብ ከማስቆጠር አንጻር ሳይሆን ከጌታ ጋር ያለንን ህብረት ፈትሸን ከማስተካከል አንጻር ይሁን።
        እነዚህ ሰዎች ሁለቱም ወደ ጌታ ቀርበዋል ሁለቱም ጌታን ፈልገውታል። የፈለጉበት ልብና የቀረቡበት አቀራረብ ግን የተለየ ነው። ይህም በውጤቱ ላይ ለውጥ አምጥቶአል። እንደሰው ስናየው በአግባቡና በስርአቱ ያስተናገደውና የተቀበለው ፈሪሳዊው ነው። በክብር ምሳ ጋብዞታል። የጋበዘውም ወደ ሌላ ሰው ቤት ሳይሆን ወደራሱ ቤት ነው። ኃጢአተኛዋ ሴት ግን ይህን ሁሉ አላደረገችም። ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ እንዲሁ ሳትጠራና ሳትጋበዝ መጣች። ይህ ፈሪሳዊ ለኢየሱስ እያደረገ ያለው የሚቆጠር የሚመካበት ነገር አለው። ይህች ሴት ግን ምንም የምትመካበትና የምትቆጥረው ነገር የላትም። ጌታን ወደቤትዋ አልጋበዘችውም (እንደሚመስለኝ በዝሙት የምትተዳደር ሴት ከሆነች ከዝቅተኛው ህብረተሰብ ስለምትመደብ ሰው የምትጋብዝበት ቤትም ያላት አይመስለኝም) ነገር ግን ራስዋን አዋርዳ ወዳልተጠራችበት ቤት ወዳልተጋበዘችበት ቤት መጣች። ለሰው ወዳልተጋበዙበት ግብዣ መሄድ የሚያሳፍር ነው። የሚገርመው ደግሞ የመጣችበት ቤት ለእንደርስዋ አይነት ሴት የማይሆን የፈሪሳዊ ቤት ነው። ይህ ፈሪሳዊ እርስዋን እንዴት እንደሚመለከታት ታውቃለች። ኃጢአተኛ ስለሆነች በህጉ አይን ነው የሚመለከታት። እንድትወገርና እንድትሞትም ሊያመቻች ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስን አምና መጣች እንጂ እንደሰው ሲታይ ወደ ሞት ቀጠና ነው የመጣችው። ወንጀል ይዞ ፓሊስ ጣቢያ መሄድን ማን ይፈልግና። ወደዚህ ቤት እንድትመጣ ያስገደዳት ግን ከዚያ ከሚፈርድባትና እስከሞት ድረስ ከሚያሳድዳት በልጦ የነገሰው የዓለም ብርሃን ስለታያት ነው። «ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።» (ዮሐ.1፡5) ተብሎ እንደተጻፈ በዚያ ድሮ ሞትና ፍርድ ብቻ ነግሶ በሚታይበት የፈሪሳዊ ቤት ይህ ብርሃን አሸንፎ ታያት። ይህን ብርሃን ተማምና ወደዚያ ጨለማ መንደር ገባች።

        ስለዚህ አቀባበላቸውን ስናይ የፈሪሳዊው ደረጃውን የጠበቀ ሲሆን የርስዋ ግን «ድንኳን ሰባሪ» እንደሚባሉት ህገ ወጥ የሚባል ነው። ይህ ፈሪሳዊ የሰራው ነገር ክፉ የሚባል ሳይሆን መልካም የሚባል ነው። ሌሎች ፈሪሳውያን ጌታን ለመግደል ሲያሳድዱትና በቃል ሊያጠምዱት ሲከታተሉት እርሱ ግን ወደ ቤቱ ጠርቶ ምሳ መጋበዙ ትንሽ ነገር አይደለም። ሌሎች ምን ይሉኛል አለማለቱም ያስመሰግነዋል። ኢየሱስን የጋበዘው ግን ማንነቱን አውቆ ሳይሆን ማንነቱን ለማወቅ እንደሆነ እናያለን። የተቀበለው አቀባበል ሰፍ ያለ ሰው አቀባበል አለመሆኑና ይህች ሴት በምትዳስሰው ጊዜ በልቡ ያሰበው ነገር ይህንን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። «ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።» (ሉቃ.7፡39) ይላል። ስለዚህ ነቢይ ይሁን አይሁን ለመለየት ነበር የጠራው አሁን ማረጋገጫውን አገኘ ማለት ነው። እውነተኛው ረቢ ኢየሱስ ግን ባልጠበቀው መንገድ ሚስጢሩን ይተርክልት ጀመር። በእውነት ኢየሱስ እውነተኛ ረቢ ነው። ምሳ ተጋብዣለሁ ብሎ እውነትን የማይደብቅ ለራሱ ሊኖር ያልመጣ ከሰማይ የሆነ ሰው በመሆኑ በሰው ልጆች መንደር የተለመደው ምን ይሉኛል ያልነካካው። ለእውነት ሊመሰክር የተወለደ። ራሱ እውነት ሆኖ እውነትን ያስተማረ ድንቅ ረቢ።

    «እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል።» (ሚክ.3፡5) የተባለላቸው ሐሰተኞች በሞሉበት ዘመን ምሳ በልቶ እውነትን የሚናገርና የሚገሰጽ እውነተኛ እረኛ እግዚአብሔር ለህዝቡ ሰጠ። በዚህ ዘመን ያሉ «ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ» (ህዝ.13፡19) ህዝብን የሚያረክሱና ለሆዳቸውና ለኪሳቸው ያደሩ አገልጋዮች ከዚህ ድንቅ መምህር ፍለጋን ይማሩ ዘንድ ይገባል። ይህ ድንቅ መምህር በክብር ምሳ የጋበዘውን ሰው ወደ ቤቱ እንጂ ወደ ልቡና ወደ ህይወቱ እንዳልጋበዘው እንዲህ በማለት አስረዳው «ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። (ሉቃ.7፡44-46) ዋው ይህ አክብሮ ምሳ ለጋበዘ ሰው እጅግ መራራ እውነት ነው። ግን እየመረረ የሚፈውስ መድኃኒት። 

      ዛሬም እንዲህ እላለሁ እግዚአብሔር ሆይ እየመረረንም ቢሆን እውነትን የሚነግሩንን እረኞችና አስተማሪዎችን አስነሳልን ይህ ይሻለናል።  

                   አሜን ይሁንልን !!!                  ካሳሁን

___________________________ ////// _________________________

የሎጥን ሚስት አስቧት

  እግዚአብሔር ቤቱን ሊያጸዳ ተዋጊውን ከጀሌው፣ ፈሪውና ድንጉጡን ከአማኙ፣ ደቀ መዝሙሩን ከምእመኑ፣ ራሱን ሊያረካ የመጣውን ራሱን ከካደው፣ ምኞት የተሸከመውን መስቀል ከተሸከመው፣ ድል ነሺውን ከድል ተነሺው ሊለይ በእውነተኛው ወንጌል ተነስቷል። ልብንና መንፈስን የሚመዝን እግዚአብሔር በመንፈሱ ቤቱን የሚያጸዳበትና ሰራዊቱን ለመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር ጦርነት የሚያሰልፍበት ጊዜ ነው። ከግብጽ የወጣው ሁሉ ወደ ከነዓን እንዳልግባ ልብ እንበል። ሁሉንም ፈጽመን ብናውቅም አንድ ነገር እንድናውቅ ይሁዳ እንዲህ ይመክረናል "ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ።" ህዝቡን ከግብጽ አገር ቢያድናቸውም ባለማመናቸው ጠፍተዋል ለመሆኑ ያለማመናቸው ዋና ምልክት ምን ነበር? እግዚአብሔር ያየላቸውን በፊታቸው ያለውን ርስት ሳይሆን የሥጋቸውን ፍላጎት የእለቱን አስቀደሙ በልዑሉም ላይ አንጎራጎሩ። ይህ ምኞታቸውም ወደ ግብጽ መለሳቸው። የተሰጣቸውን ቃል ሊታዘዙት አልወደዱም "ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ።" በልባቸው ወደ ግብፅ ስለተመለሱ ጌታን መከተል አልቻሉም።

ደቀመዝሙር ማለት ወደኋላ የማያይ ጌታውን ብቻ እየተከተለ ወደፊት የሚሄድ ነው። "ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም" ተብሎ ተፅፎአልና።

ጌታ የሎጥን ሚስት አስቧት ያለን ለምን ይሆን? ከወጡ፣ ካመለጡ ፣ከዳኑ በኋላ መጥፋት ስላለ አይደለምን? የሎጥ ሚስት ወደኋላ አልሄደችም ግን በልቧ ወደ ኋላ ሄደች። ጌታ አካላችን ያለበትን ሳይሆን ልባችን ያለበትን ያያል፡ ደቀ መዝሙር የሚያደርገን፡- የልብ እምነት፣ የልብ መገረዝ፣ የልብ ውሳኔና ጭካኔ እንጂ በውጭ የምናሳየው ግብዝነት አይደለም።

ጌታን ስንከተል በእግራችን ሳይሆን በልባችን እየተከተልነው መሆኑን ይመዝነናል። «የፈራና የደነገጠ ይመለስ» ሲል በውስጣቸው ያለውን የመመለስ ፍላጎት አይቶ አጸደቀላቸው እንጂ የተመለሱትስ «ተመለሱ» ሳይባሉ ነው። ልባቸው ያለው ቤታቸው ከሆነ ድሮውንስ መቼ መጡና ?

ስለዚህ እግዚአብሔር ተመለሱ ያለው አካላቸውን እንጂ ልባቸውማ ድሮም አልመጣም። ይህም የሚያሳየን እውነተኛ ደቀመዛሙርት ልባቸውን በዓለም አስቀምጠው ነፍሳቸውን እየተንከባከቡ ባላቸው ላይ እንዲጨመርላቸው ጌታን ለመጠየቅ ወደ የጸሎት ቤቱ የሚጎርፉት ሳይሆኑ ሁሉን (አዎ ሁሉን) ትተው የተከተሉት ናቸው።

ስለዚህ ሁሉንም ትተን ለመከተል ጌታ ይርዳን !!! ተባረኩ

 ካሳሁን

-------------------------------/////------------------------------------

መተው

      ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ።(ማር 10:29)

     መቼም ከተውነው ይልቅ የሰበሰብነው ይበልጣል ። ስለ ክርስቶስና ስለ ወንጌል መተውን ሳይሆን ማትረፍን እየተለማመድን ነው። ክርስቶስ የሚተውለት ሳይሆን የሚተረፍበት እየሆነ ከመጣ ቆየ። እንዲህ ብታደርግ ይህን ታገኛለህ ፣ እንዲህ ብታደርግ ኑሮህ ይሞላል የሚል ዘመንኛ ስብከት ወንጌልንና ክርስቶስን እያሰረ በርባንን በቤቱ ውስጥ እያስለቀቀ ይገኛል። ጌታ በርባኖችን በቤቱ ሲያገኝ የሚለን ቤቴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት ነው። በብዙዎቻችን ህይወት ክርስቶስ ስንት ስንተኛውን ስፍራ እንደያዘ ባላውቅም 100% በህይወታችን ስፍራ ከሌለውና 99 % እንኳ አግኝቶ ቢሆን በጣም ከስረናል።

     በዚህ ዘመን አስጨፋሪዎቻችን 40% ትንቢት ተናጋሪዎቻችን 40% ኑሮአችን 20% ህይወታችንን ይዞብን ክርስቶስ ስፍራን ያጣበት ሁኔታ ነው ያለው። ዛሬም የክርስቶስ ድምፅ እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ የሚል ነው። ምን ይሆን እደጅ ያቆመው ብለን ቆም ብለን አስበነው ይሆን? ወይንስ ወንጌልን አምነው ላልዳኑት እየጠቀስነው ይሆን? ጌታ ይህን ቃል የተናገረው ላልዳኑት ነበርን? እስቲ ክፍሉን እንየው: ( ራእይ 3:14) ላይ ይገኛል ይህ ቃል የተነገረለት ደግሞ ያላመነው ሳይሆን በሎዶቅያ የምትገኝን ቤተክርስቲያን ነው። ክርስቶስን እደጅ ካቆሙት ምክንያቶች ውስጥ ዋናው በራድ ወይንም ትኩስ አለመሆንና በራስ ሀብታም ነኝ ምንም አያስፈልገኝም ብሎ መኩራራት ነው። ምናልባት የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን እደጅ ማቆሟን አታውቀው ይሆናል ። ዛሬም በዚህ ዘመን የሚሆነውን ስንመለከት በቤቱ ደጅ እንዳቆምነው ብናስብ ለንስሀ ይረዳናል።

    አገልግሎት ለኑሮ ማሻሻያና ለክብር ለዝና ማግኛ እንጂ ክርስቶስን ለመስበኪያ ከሆነ ቆየ። በቤተክርስቲያን ሰላም የለም። አገልጋይ ከአገልጋይ ሰላም የለም ። በአንድ ከተማ ዘፋኝ ወይንም ጠንቋይ መምጣቱ ሳይሆን አገልጋይ መምጣቱ የሚያስደነግጣት ቤተክርስቲያን ናት። ስህተትን የስህተት ትምህርትን የምታስታውሰው ያለንበትን አለም ዘመኑን በመመርመርና በማስተዋል ሳይሆን አገልጋይ ከተማ ውስጥ አለ ሲባል ነው። በቤት ውስጥ አገልጋይን መቀበል ጠላትን የመቀበል ያህል ወንጀል ነው ። ለነገሩማ ጠላትህ ቢራብ አብላው ቢጠማ አጠጣው ነበር ትዕዛዙማ! ጳውሎስ ለገላትያ አማኞች በአይናችሁ ፊት ክርስቶስን ሳልኩ ያውም እንደተሰቀለ ብሎ ነበር በገላትያ 3 :1 ላይ። እልፍ ብሎ በምዕራፍ 4:19 ላይ የጳውሎስ ምጥ ዳግመኛ ክርስቶስ እስኪሳል እንደሆነ ቃሉ ይመሰክራል ። ራሳችንን በዲቪዲ እና በከባባድ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት ክርስቶስ በሞተለት ህዝብ ላይ የምንስል ሽልማት ይኖረን ይሆን? ለመሆኑ ይህን ጹሑፍ እያነበብን አንብበን ለመጨረሳችን ምን ዋስትና አለን ይሆን? በእግዚአብሔር ፊት የምንኖር ነንና እስቲ እድሜያችንን በእግዚአብሔር አቆጣጠር እናስላው ምናልባት ካነቃን።

    በ2ኛ ጴጥሮስ 3:8 ላይ ወዳጆች ሆይ እንዳትረሱ በማለት የነገረን ምስጢር ቢገባን ይህን ሃላፊ አለም በጠላነው ነበር ። በእግዚአብሔር ፊት ሺህ አመት እንደ አንድ ቀን ከሆነ በምድር ላይ ትልቁን እድሜ የኖረው ማቱሳላ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ አመት ነበር የኖረው ። በእግዚአብሔር አቆጣጠር ስናሰላው በፊቱ አንድ ቀን ያደረ የለም ። በሰው ብልጠት አንድ ቀን የማናድር ምናለበት በክርስቶስ ዘላለማዊ ስጦታ ብንረካ? እኔ ከምሰጠው የሚጠጣ አይጠማም አልነበር ያለው? ዘላለም ከሰው እየጠጣን ከምንባዝን ምነው ከእርሱ ጠጥተን ብናርፍ? ማስተዋልን ይስጠን! አሜን!

                    ጌታ ይባካችሁ።

    ካሱ ቦስተን

-----------------/////-----------------

እናንተም እንዲሁ በእጄ ውስጥ ናችሁ።

 

     ኤርምያስ በ18ኛው ምዕራፉ በቁጥር 5 ላይ እንዲህ በማለት አስፍሮልናል የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ሸክላ ሠሪው እንደሚሠራው፣ እኔ በእናንተ ላይ መሥራት አይቻለኝምን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ጭቃው በሸክላ ሠሪው እጅ እንዳለ፣ እናንተም እንዲሁ በእጄ ውስጥ ናችሁ።

 

       እግዚአብሄር አምላካችን ገና በመልኩና በአምሳሉ ሲፈጥረን ከመሬት አፈር እንደፈጠረን ሁላችንም አንዘነጋውም ዛሬም ይኸው አምላካችን እናንተ በእጄ ውስጥ ያላችሁ ተሰርታችሁ ያላለቃችሁ ጭቃ ናችሁ እያለን እያስታወሰን ነው። መቼም ሰው ነንና የተሰራንበትን ረስተን በማን እጅ እንዳለን ረስተን ኮራ ኮራ ለማለት እንሞክራለን ። ልክ ከአልማዝና ከዕንቁ እንደተሰራ ሰው ! የተሰራንበትን አፈር እንክዋን ለመርገጥ የተጸየፍን ብዙዎች ነን። ዛሬ ግን ልንገራችሁ። አንተም አንቺም እኔም ከአፈር የተገኛችሁ ናችሁ ገና ሰርቼ አልፈጸምኳችሁም እንደፈለኩት አድርጌ ልሰራችሁ በእጄ ላይ ናችሁ ይለናል እግዚአብሄር። ሸክላ ሰሪው እያፈረሰ እያስተካከለ ሞልድ እያረገ በእሳት እያቃጠለ ጥንካሬ እንዲያገኝ በማለስለሻ እያስተካከለ በቀለም እያሰማመረ እያስዋበ እንደሚቀርጻት በእጁ እንደፈለገ እንደሚያደርጋት ሸክላ: የናንተ ነገር የልጆቻችሁ ነገር የትዳራችሁ ነገር የኑሮአችሁ ነገር ሁሉ በእኔ እጅ ነው ያለው ሁሉንም ሰርቼ አልጨረስኩትም ለእኔ ተዉልኝ ይላል እግዚአብሄር። በእናንተ የጀመርኩት መልካም ስራ አለኝ ይላል እግዚአብሄር። በልጆቻችሁ ልሰራ ያቀድኩት ስራ አለኝ ተስፋ አትቁረጡ ይላል ለምን በኔ ላይ እንዲህ አይነት ፈተና ደረሰ?? ለምን ለምን ለምን ??? መቼ ነው የምጎበኘው?? መቼ ነው የምታየው? እግዚአብሄር አለህ ወይ?? ለምን ትላለህ/ትያለሽ ??

ለምን የዛሬውን ብቻ ታያላችሁ አሻግራችሁ ትኩር ብላችሁ የወደፊታችሁን ተመልከቱ ስለናንተ የማስበው ሃሳብ የመልካምና የበጎ ፍሻሜውም ያማረ መሆኑን ነግሪያችሁ የለምን ይላል እግዚአብሄር።   

      መንፈሳዊ ቤት አድርጌ ልሰራችሁ ላበጃጃችሁ ልቀርጻችሁ የምችለው እኔ ነኝ እያለን ነው ። በራሳችሁ አንዳችም ልታደርጉ አትችሉም እናንተ እራሳችሁን ለመስራት አቅሙ ችሎታውም የላችሁም ምክኒያቱም ያላችሁት በኔ እጅ በመዳፌ ውስጥ ነው ምኖሪያ ቤቴን ላሳምረው ውስጡ ያለውን ቆሻሻ ላስወግድ የምችለው በውስጡ የተሸሸጉትን የተደበቁትን ደባል የሆኑትን እየገረፍኩ ላስወጣ ከዚያም ቤቴን የጸሎት ቤት ላደርገው የመንፈሴ ማደሪያ የራሴ ብቻ መኖሪያ ላደርገው የምችለው እኔው እራሴ ነኝ እናንተ ብዙ ለፋችሁ ደከማችሁ እናንተ ከላይ ያለውን በቀለም ለማሳመር ሞክራችኋል እርሱም ያለሞያተኛ የተቀባን ቀለም ይመስል ተዥጎርጉሯል

ስለዚህ ያቃታችሁን ነገር ለዓመታት የተሸከማችሁትን ማንኛውንም ሸክም ላራግፍላችሁ ከነሸክማችሁ አትመላለሱ ለእኔ የሚያቅተኝ አንዳችም የለም እኔ ኤልሻዳይ ነኝ ወደ እኔ ቅረቡ እኔን ፈልጉ ለነፍሳችሁ እረፍትን ለህይወታችሁም ውበትን ታገኛላችሁ። 

በእኔ እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ ይላል እግዚአብሄር።

 ካሱ ቦስተን

========////=========

ቅዱሳን ሁኑ !

  ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።  

(1ኛ የጴጥሮስ መልእክት1:15-16)

(ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:20-23)

 

ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን፦ ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም። በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡

እግዚአብሄር እኔ በአህዛብ ፊት እናንተን የምሰራው በእናንተ ውስጥ ለመኖር የምፈልገው ከነርሱ ውጡና የተለያችሁ ሁኑ እርኩሱንም ነገር አትንኩ ብያችሁ ነበር ነገር ግን እናንተ በመሃከላቸው ሆናችሁ ቅዱሱን ስሜን አረከሳችሁት ስለዚህ እኔ እንደሎጥ እራራላችሁና እጃችሁን ይዤ አወጣችኋለሁ ለራሴ ለቅዱሱ ስሜ ስል እቀድሳችኋለሁ ያኔ እናንተን ስቀድስ መልካም አድርጌ ስሠራችሁና በናንተ ውስጥ ስኖር አህዛብ እኔ እግዚአብሄር እንደሆንኩ ያውቃሉ እኔ እራሴ ስሜን አስከብራለሁ እናንተን እቀድሳለሁ እንደገናም በእናንተ እቀደሳለሁ ይላል ይህን የማደርገው ግን እናንተ ስለሰራችሁት ስለመልካም ስራችሁ ሳይሆን ስለራሴ ቅዱስ ስለሆነው ስሜ ነው ይላል ምክኒያቱም እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን እንድትሆኑ ስለምፈልግና እኔንም ማየት የምትችሉት በቅድስና ስትኖሩ ስለሆነ ነው

 

እንግዲህ መንፈሳዊ ቤት ሆናችሁ እንድትሰሩና እኔ እንድኖርባችሁ ይህን ከዚህ የሚቀጥለውን በመካከላችሁአደርጋለሁ ይላል እግዚአብሄር

 

ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። (ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:24-28)

 

አሜን አሜን አሜን!!!  

 ካሱ ቦስተን

========================================

አቋማዊ (positional) ቅድስና ምን ማለት ነው?

 

መቀደስ ማለት ለንጽህና መለየት ማለት ነው። ሃጢአተኞች በእግዚአብሔር ጸጋ አማካኝነት በተሰጣቸው እምነት በጸጋው በኩል ከሃጢአት ሲድኑ ይቀደሳሉ (ኢፌ. 2:8-9)፤ ማለትም ለንጽህና ይለያሉ። የመዳን (የድነት) ሦስት “ደረጃዎች” አቋማዊ መቀደስ (positional sanctification)፣  ቀጣይነት ያለው መቀደስ (progressive sanctification)፣ እና የመጨረሻው መቀደስ (final sanctification) በመባል ይጠራሉ።. በሌላ አነጋገር፣ አቋማዊ ቅድስናችን በክርስቶስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ፊት ስላልን ጽድቅ (justification) ሲያውራ፣  ቀጣይነት ያለው ቅድስናችን ደግሞ በምድር ላይ ስለሚኖርን መንፈሳዊ ብስለት (spiritual maturity) ያወራል። የመጨረሻው መቀደስ የሚያወራው ደግሞ በትንሳኤ ስለምንቅበለው ክብራችን (glorification) ነው።

ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛችን በተቀበልን ቅጽበት አቋማዊ ቅድስናን አግኝተናል፤ ወይም ጸድቀናል። ይህም ማለት በኃጢአታችን ምክንያት ሊደርስብን ይችል ከነበረው ቅጣት ሙሉ በሙሉ ድነናል ማለት ነው። ይህ ቅድስና የአንድ ጊዜ ክንውን እንጂ ሂደት አይደልም። ይህ ቅድስና እየተሻሻለ ወይም እያደገ የሚሄድ አይደልም፤ ፍጹምና የመጨረሻ እንጂ። አቋማዊ ቅድስናችን ማለት በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ምክንያት ያገኝነው ቅድስና ማለት ነው። ስለዚህ ቅድስና ስናወራ እያወራን ያለው ስለ ሰማያዊው ቅድስናችን፣ አሁን ሰለ ማይታየው ነገር ግን ወደፊት ሊገለጥ ስላለው ቅድስናችን፣ ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ስለ ተሰወረው ቅድስናችን፣ ወይም በክርስቶስ ዳግም ምጻት ሊገለጥ ስላለው ቅድስናችን ነው። ባጭሩ፣ ይህ ቅድስና ክርስቶስ ስለ እኛ በአብ ፊት የሚታየው መታየት ማለት ነው። ስለ አቋማዊ ቅድስናችን ስናወራ የምናወራው በእግዚአበሔር ፊት ተቀባይነት ስላገኘውና ፍጹም ስለሆነው ቅድስናችን ነው። አቋማዊ ቅድስናችን በክርስቶስ ለእግዚአበሔር የተለየን ሕዝቦች መሆናችንን ያሚያብስር እንጂ አሁን በምድር ላይ ስላለን መልካም ባሕሪይ አያወራም። ጉዳዩ ሰለ ስፍራችን እንጂ ስለ ባሕሪያችን አይደለም። አቋማዊ ቅድስና የሚያወሳው እኛን አስመልክቶ በሰማይ ስለተከናወነው ለውጥ እንጂ በምድር ስላልን ስነ-ምግባራዊ ለውጥ አይደልም።

በምድር ስላልን ስነ-ምግባራዊ ቅድስና ስናወራ ደግሞ እያወራን ያለንው ‘’ቀጣይነት ስላለው መቀደስ (progressive sanctification)” ነው። ይህ ቀጣይነት ያለው ቅድስና፣ ከኃጢአት ልምምድ (practice of sins) እና ከኃጢአት ኃይል (the power of sin) የመዳን ሂደትን ያመለክታል። ይህ የቅድስና ደረጃ አንደ አቋማዊ ቅድስና የአንድ ጊዜ ክንውን ሳይሆን በምድር በሕይወት እስካልን ድረስ ያሚቆይ የቅድስና ጉዞ ወይም ሂደት ነው። ቀጣይነት ያለው ቅድስና ያሚያወራው ስለ ተግባራዊ ቅድስና ወይም ስለ ምግባራዊ ቅድስና ነው። በሌላ አነጋገር ይህ ቅድስና የሚያወራው በምድር ላይ ስላልን የኑሮ ቅድስና ወይም ተጨባጭ ቅድስና ነው።

በዚህ ምድር ላይ ያለን የቆይታ ጊዜ ሲያበቃ ማለትም ነፍሳችን ከስጋችን ሲለይ በመጨረሻው መቀደስ (final sanctification) እንቀደሳለን። በዚህኛው የቅድስና ደረጃ ደግሞ ፈፅሞ ከኃጢአት መገኘት (presence of sin) እንድናል ማለት ነው። በዚህ ቅድስና ውስጥ ስንገባ የመጨረሻውን ክብራችንን እንቀበላለን።    

ቀጣይነት ስላልውና ስለ መጨረሻው የቅድስና አይነት እዚህ ላይ ገታ እናድርግና የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳይ ስለሆነ ስለ አቋማዊ ቅድስና ተጨማሪ ጉዳዮች እናውራ። ከላይ እንደተገለጸው ይህ አይነቱ ቅድስና መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ልብ ውስጥ የሚያከናውነው የአንድ ጊዜ ድርጊት ነው። በድነት ወቅት፣ አማኞች ኃጢአተኛ መሆናቸውን ተረድተው ይናዘዛሉ፤ በራሳቸው ማንኛውም ሥራ ራሳቸውን ለማዳን እንደማይችሉ ይገነዘባሉ፤ አዳኝ እንደሚያስፈለጋቸው ይረዳሉ፤ ክርስቶስ ለኃጢአት ክፍያ በመስቀል ላይ የከፈለውን መሥዋዕት ይቀበላሉ፤ እንዲሁም በኢየሱስን ትንሣኤም ያምናሉ።  በዚያ ቅጽበት፣ አማኞች ከድቅድቅ ጨለም ወደሚያስደንቅ ብርሃን ይሻገራሉ። “በእምነት ይጸድቃሉ” ( ሮሜ 5:1 ) ከእግዚአብሔር አንጻር ስፍራቸው (አቋማቸው) ለዘላለም ይቀየራል። የአዲስ መንግስት ዜጎች ይሆናሉ። “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” (ቆላ. 1:13 )።

አቋማዊ ቅድስና የመንፈሳዊ አድራሻ ለውጥ ማድረግ ማለት ነው። ቀድሞ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚጠብቀን ሃጢአተኞች ነበርን። ስፍራችን፣ መለዮአችን ወይም አቋማችን ይህ ነበር። በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ባመንን ወቅት ግን ባገኘነው አቋማዊ ቅድስና ምክንያት አድራሻችን፣ መለዮአችን ለአንዴና ለመጨረሻው ተቀይሯል፡፡ አሁን የቁጣ ለጆች ሳንሆን የተወደድን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ሃጢአተኞች ሳንሆን በአግዚአብሔር ፊት ፍጹማን ነን። ይህ የአቋማዊ ቅድስና ውጤት ነው፤ ማለትም የኢየሱስ የመስቀል ስራ ውጤት። የመንፈሳዊ አድራሻ ለውጣችን የክርስቶስ አካል ብልቶች እንድንሆን (1ቆሮ. 12:27 )፤ የርስቱ ወራሾች አንድንሆን (1ጴጥ. 2:9 )፤ አዲስ ፍጥረት አንድንሆን (2 ቆሮ. 5:17 )፤ ለኃጢአት አንድንሞት (ሮሜ 6:2 )፤ እና የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች አንድንሆን (2 ጴጥ. 1:4) አድርጎናል። ድነት የመንፈስ ቅዱስ ፍጹም ስራ ስለሆነ በመንፈሳዊው ስፍራ የተደረገው መነፈሳዊ የአድራሻ ለውጥ በአማኙ ምግባር ምክንያት ዳግመኛ ያማይቀለበስ ለውጥ ነው። የአማኙ መንፈሳዊ አድራሻ ፈጽሞ አይቀየርም ወይም አይለውጥም ወይም አይጠፋም ወይም ቀድሞ ወደነበረበት አይመለስም። ይህን አቋማዊ ቅድስና በገዛ እጃችን መለወጥ አንችልም። በተለወጠው አዲስ አድራሻችን ለዘላልም እንንኖራለን።  አቋማዊ ቅድስና የእግዚአብሔር ስራ ነው። እግዚአብሔር “ከእርሱ (ከክርስቶስ) ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” (ኤፌ. 2:6 ) የሚለው አረፍተ ነገር በሃላፊ ጊዜ መቀመጡን እናስተውል። ስፍራችን ተቀይሯል። አቋማዊ ቅድስና ማለትም ይህነኑ ማለት ነው። እርሱ ማለተም እግዚአብሔር አስቀምጦታልና አማኝ በዚህ ስፍራ ለዘላለም ይኖራል። አቋማዊ ቅድስና በእኛ ስሜት ላይ የተመሰረት ባለመሆኑ በሰማያዊ ስፍራ ያለነው ስለተሰማን ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሚያረጋግጠው የድነት እውነታ ስለሆነ ብቻ ነው። ይህንንም በእምነት እንቀበላልን። ዛሬ በምድር ላይ ያለን ተግባራዊ ልምምድ ከመንፈሳዊ አድራሻችን አንጻር ያማይጣጣም መስሎ በሚሰማን ወቅትም ቢሆን እንኳ ስፍራችን (አቋማዊ ቅድስናችን) አይቀየርም፤ ስሜታችን የእግዚአብሔር ቃል ያወጀውን መነፈሳዊ እውነታ አይቀይረውም። አቋማዊ ቅድስና ያሚያስተላልፈውን መንፈሳዊ እውነታ በአግባቡ ላልተረዳ ሰው አማኙን መረን የሚለቅ ትምሕርት ሊመስል ይችላል።  በመሰረቱ፣ አቋማዊ ቅድስና አማኙን ቀጣይነት ወዳለው ቅድስና የሚመራ የአዲስ ሕይወት መነሻ እንጂ የአሮጌው ሕይወት ልምምድ ላይሰንስ (ፈቃድ) አይደለም። ይህም በአማኙ ሕይወት ውስጥ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ የመልካም ምግባር ፍሬን ያፈራል ማለት ነው። ዳግም ልደት ያገኙ አማኞች አዲሱ ተፈጥሯቸው ግድ ያሚላቸውን የአዲሱን ተፈጥሮ ባሕሪይ መለማምድ ይጀምራሉ። የመንፈሳዊ አድራሻ ለውጣቸው በምድር ላይ በሚኖሩት የእለት ተእለት ሕይወታቸው ላይ አወንታዊ ለውጥ ማሳድር ይጀምራል። ይህም በየእለቱ እያደገ በሚሔድ የባሕሪይ/የስነ-ምግባር ለውጥ እየታየ ይሄዳል (1ጴጥ.1:15-16)። ይህንንም ቅድስና ቢሆን፣ አቋማዊ ቅድስናን በኛ የሰራው መንፈስ ቅዱስ በታዘዝነው መጠን በእኛ ውስጥ የሚያደርገው ይሆናል። ለማጠቃለል ያህል፣ አቋማዊ ቅድስናችንን ስናገኝ፣ ቀጣይነት ያለው የመቀደስ ሂደት በሕይወታችን ተግባራዊ መሆን ይጀምራል። ቀጣይነት ያለው መቀደስ ክርስቶስን እየመሰሉ የማድግ የሕይወት ዘመን ሂደት ነው። መንፈስ ቅዱስን በታዘዝነው መጠን እና ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር በፈቀድንለት መጠን ክርስቶስን በመምሰል እናድጋለን (ሮሜ. 8:29፤ 2ቆሮ. 3:18)። አቋማዊ ቅድስናችንን ስናገኝ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል እንደመሳሪያነት በመጠቀም ይህንን ቀጣይነት ያለውን የመቀደስ ሂደት በሕይወታችን እውን ያደርጋል (ዮሐ. 17:17)። ምግባራዊ ቅድስናችን የሰማያዊ ቅድስናችን ነጸብራቅ እስኪምስል ድርስ እለት ተእለት ክርስቶስን እየመሰልን እናድጋልን (1ዮሐ. 3:2)።

======================================

እግዚአብሄርን የምትሸከሙ ናችሁ !

 

     እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ (1ጴጥ 2:9)

 

   ይሄውላችሁ ወገኖች እኛ ዳግም ስለተወለድን፣ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነን፤  “… እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ እንደሚል ቃሉ የእግዚአብሄርን ሃይል እንሸከማለን እናስተላልፋለንም፡፡ ከጳውሎስ አካል በተወሰደው ልብስ ላይ የእርሱ ሃይል እንደተላለፈው ሁሉ (ሐዋ 19፡ 11-12)፣ ከእኛ የሚወጣ ማንኛውም ነገር ወይም እኛ የነካነው ነገር ሁሉ፣ የእግዚአብሄርን ሃይል ይካፈላል፡፡ በእንደዚያ ዓይነት መካፈል ውስጥ ደግሞ ትልቅ ብቃት ይመጣል፡፡    

 

    ከእኛ ጋር ተነካክቶ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት በላዩ ላይ የማይቀር ምንም ነገር የለም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሄርን መለኮታዊ መገኘት የምንሸከም፤ እኛ እግዚአብሄርን የምንሸከም እቃዎች ነን አዎ ነን ዛሬ በጣም እናስተውል እግዚአብሄርን ከነሙሉ ክብሩ የምንሸከም ቅዱስ ካህናት ነን ፡-

 

“… እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፥ እልፍ በሉ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፥ ከመካከልዋ ውጡ፥ ንፁሐን ሁኑ።(ትንቢተ ኢሳይያስ 52፥11) “ እንደሚል፡ እኛ የእግዚአብሄር ዋና መስርያ ቤት ማለትም ስራውን የሚሰራበት  ዋና ቦታ ነን፤ የእርሱን ፍቅር በእኛ በኩል ያሳያል፤ ይገልጣልም፡፡ የእርሱን ጸጋና መለኮታዊ መልካምነት የሚገልጥበት ስፍራው እኛ ነን ፤ መክፈቻ ጥቅሱን እንደገና አንብቡ፡፡ ለምሳሌ ቃሉን ካንድ ሰው ጋር እየተካፈልን ከነበረ፣ በቃላችን ሃይሉን ወደዛ ሰው ልናስተላልፍ እንችላለን ፡፡ ፍቅሩ፣ ፍህራሄውና መገኘቱ ከእኛ ወደነሱ ይፈሳል፤ የፍቅሩንና የጽድቁን ንቃተ ህሊናም ያመጣላቸዋል፡፡ በጌታ ኢየሱስ እና ከሐዋርያቶቹ አገልግሎት የምናየው ይህንን ነው፡፡ ያደረጉትን የሚያስደንቅ ድንቅና ተአምራት ለእኛ የተጻፉት፣ እንድናነባቸው እና እንድናውቃቸው ብቻ ሳይሆን፤ እኛም በጊዜያችን በዛው መንፈስ ያንን የእርሱን ሃይል ማድረግ እንደምንችል እንድናውቅ እና እንድንነሳሳ ነው፡፡

 

   የእግዚአብሄርን መለኮታዊ መገኘት ተሸካሚ እንደሆንን  እንወቅ፤ የእርሱ ክብር የሚወጣበት መሳርያ ነን፡፡ በቋሚነት በየዕለቱና በየቀኑ በየጊዜው በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ የሚፈለግበትም አንዱ ምክንያት ይህ ና ይህ ብቻ ነው (ኤፌ 5፡18)፤ በመንፈስ ስንሞላ የእርሱ ኃይል ሰላም ደስታ እረፍት ፍቅር ቸርነት ወዘተ ተትረፍርፎ በእኛ በኩል ወደሌላው ይፈሳል ሃሌሉያ !! አሜን ፡፡ ስለዚህ እራሳችንን የምናይበት የእይታ መነጽር ይስተካከል እላለሁ ተባረኩልኝ  አሜን አሜን ፡፡

ካሱ ቦስተን

_________________//___________

በጌታ ብርሃን ናችሁ !

 

       “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። (ኤፌሶን 5:8-13)።

   ወገኖቼ የእግዚአብሔር ቃል እናንተ የአለም ብርሃን ናችሁ ሲል ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የተሰተካከለ የጽድቅ እምነት ያገኝነው እኛ ክብርን፤ሕይወትንና ኃይልን ከእርሱ በቀጥታ ተቀብለን አለምንም መከልከል ስለምናስተላልፍ ነው አለም ክርስቶስን የምታየው በኛ ነውና አለበለዚያ ግን የአለም ብርሃን ሳንሆን የጋን መብራት ነው የምንሆነው ። በዚህ አለም በምንኖርበት ጊዜ በኑሯችን ሁሉ ብርሃን መሆን አለብን። “የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና” (የሉቃስ 16:8)። ወገኖቼ እኛ ከነርሱ ይልቅ ልባሞች መሆን ይገባናል። አባታችንን መምሰል። እንደ ብርሃን ልጆች በብርሃን፥ በጥበብ፥ በእዉቀት በምህረት፥ በርህራሄ፥ በፍቅርና በጽድቅ መመላለስ ይኖርብናል። ክርስቶስ የአለም ብርሃን ነው። በብርሃኑ ብርሃን እናያለን። እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ነን። የክርስቶስን ጽድቅ ለብሰናል። በፍቅር እንኑር። በቅድስና እንኑር። ወንጌልን እንስበክ። ህይወቱ በህይወታችን ይገለጥ። ጌታ ራሱ “እናንተ የአለም ብርሃንና አለሙን የሚያጣፍጥ ጨው ናችሁ ብሎናል። ብርሃን ናችሁ ካለ ብርሃን ነህ፥ ብርሃን ነሽ እንጂ አሁድ እሁድ እየተሰባሰብን ክርስትና ክርስትና የምንጫወት አይደለንምም መሆንም የለብንም። ቃሉ የታመነ ነው።

    መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን “እግዚአብሔር እርሱ ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም።” (1ዮሐ. 1፡5) ብርሃን የሕይወት፣ የተስፋ፣ የእውቀት፣ የጽድቅ... ወዘተ ምልክት ነው። ጨለማ ደግም የሞት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የድንቁርና፣ የሃጢያት... ወዘተ ምልክት ነው። እግዚአብሔር ባለበት ሁሉ ያለው ሕይወት ነው፣ ተስፋ ነው፣ ጽድቅ ነው፣ መገለጥ ነው። እግዚአብሔር እርሱ ብርሃን ነው ደግምም በብርሃን ውስጥ ይኖራል።

 

       በወንጌል በማመን የእግዚአብሔርን ሕይወት ስንካፈል በእግዚአብሔር ብርሃን ውስጥ እንገባለን። በዚህ ብርሃን ውስጥ ስንሆን ሞት አያስፈራራንም። ይህ ብርሃን ባለበት ጨለማ ስፍራ የለውም። ብርሃኑ በጨለማ ይበራል። ይህ ብርሃን የሚዋጋንን ማንኛውንም የጨለማ ሃይል ይገልጣል። ብርሃኑ ሲገዛ ጨለማው ስፍራ ይለቃል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ብርሃንና ጨለማ አብረው ሊቆሙ አይችሉም። በእግዚአብሔር ብርሃን እየተመላለስን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ለመግባት አንችልም። በእግዚአብሔር ብርሃን ውስጥ እያለን በሃዝንና በትካዜ ውስጥ አንሰነብትም። ዳዊት እንደዘመረው እግዚአብሔር ብርሃናችን ሲሆን የሚያስፈራን፣ የሚያስደነግጠን አይኖርም። (መዝ. 27፡1)

 

ስለዚህ ዛሬም እራሳችንን የምናይበት የእይታ መነጽር ይስተካከል እላለሁ ተባረኩልኝ  አሜን አሜን ፡፡

=======////=======

እናንተ የምድር ጨው ናችሁ !

       እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ማቴዎስ 5፡13

የሰው ልጅ ጨውን ለብዙ መቶ ሺህ ዓመታት ለተለያየ አገልግሎት ሲተቀምበት ኖሯል አሁንም እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡  ጨው በዓለም ላይ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከ14,000 በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶች መዋሉን ሰለጨው ጥቅሞች በተለያዩ ድህረገጾች ላይ ተገልጾ ይገኛል፡፡

     ስለጨው ጥቅምና ጉዳት ከታች በሚመለከቱት ድህረ-ገጼ በመግባት ጤናችን በሚለው አውድ ስር የሚያገኙት ሲሆን እንዲያነቡት አበረታታዎታለሁ፡፡

የዛሬው መልዕክቴ ይህን የጨውን ጥቅም ለመዘርዘር ሳይሆን ለምንድነው ጌታ እኛን በጨው የመሰለን ? ለዚያውም የምድር ጨው ናችሁ ሲለን ምን ለማለት ፈልጎ ነው?  የሚለው ነጥብ ላይ ማተኮር ያስፈልገናል ስለዚህ በትንሹ ጨው ለምግብ ከሚሰጠው ጥቅም ጋር አያይዘን እንመልከተው ፡፡

      ምግብ ለመበላት ሊጣፍጥ ይገባዋል፡፡ ምግብ የማይጣፍጠው ከሆነ ሰው ለመብላት አይበረታታም፡፡ ምግብን ለማጣፈጥ የሚጠቅመው ዋነኛው ነገር ደግሞ ጨው ነው፡፡ ጨው የምግብ ጣእምን ሰብሰብ የማድረግ አቅም አለው፡፡ ጨው የምግብ ጣእምን ወደ አንድ ደረጃ የማምጣት ችሎታ አለው፡፡  ጨው ምግቦችን ጣዕማቸው ሳይቀይር የማቆየት ብቃት አለው፡፡ ጨው የሚስብ ነገር አለው፡፡ ጨው በሁሉ ሰው ታዋቂና ተፈላጊ ጣእም አለው፡፡ ጨው በሁሉም አይነት ምግቦች ላይ ቀይ ወጥ: አልጫ ወጥ: ጎመን ወጥ: ሰላጣ: ፍርፍር: ወ.ዘ.ተ. ጨው የማይገባባቸው የምግብ አይነቶች የሉም፡፡ ምንም ያህል ድግስ ተደግሶ የሚያጣፍጥ ጨው ከሌለው ድግሱ ተመጋቢ ያላገኘ ድግስ ይሆንና የተዘጋጀው ምግብ ወደቆሻሻ መጣያ ስፍራ መወሰዱ አይቀሬ ነው ፡፡

     ልክ ከእግዚአብሄር ጋር በክርስቶስ የመስቀል ስራ እንደታረቅን ወደ መንግስተ ሰማያት ያልገባነው በምድር ላይ ወሳኝ ስራ ስላለን ነው፡፡ ስለ   እኛ ስለተከታዮቹ ኢየሱስ ሲናገር የምድር ጨው ናችሁ ይላል፡፡ ጨው የምግብን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው እኛ የምድርን የህይወት ደረጃ ከፍ እናደርገዋለን፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የመፍራት ከፍ ያለ የህይወት ደረጃ ካላሳየን ምድር እግዚአብሄርን ፈርቶ የሚያስፈራራው ምሳሌ አይኖረውም፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ህይወት ምሳሌ ካልሆንን ምድር የእግዚአብሄርን መልክ ማየት አትችልም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን ስለማክበር ሞዴል ካልሆንን አለም እግዚአብሄር እንዴት እንደሚከበር ምንም ፍንጭ አይኖረውም፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ በራስ የማይቻል ነገር በማድረግ እግዚአብሄር እንዳለ ካልመሰከርን ስለእግዚአብሄር መኖር የሚመሰክር ሰው አይኖርም፡፡

       ጨው የምግብን የተለያየ ጣእም እንደሚሰበስበውና አንድ ወጥ ጣእም እንደሚሰጠው እኛም የምድርን ትኩረት ወደ ሰማይ የምናመለክተው እኛ ነን፡፡ እንዲሁም ከሞት በኋላ ህይወት አንዳለ አድርገን በመኖር ሌሎችንም የምናነቃውና ምድራዊ ህይወት ጊዜያዊ እንደሆነ አድርገን በመኖር ሌሎቹ ለዘላለማዊ ህይወት እንዲዘጋጁ የምናስጠነቅቀው እኛ ነን፡፡ በሰማይ ጌታ እንዳለው ሰው በመኖር ራስን በመግዛትና በዲሲፒን ኑሮ ክርስትና እንደሚቻል ፣ እግዚአብሄርን ማስደሰት እንደሚቻልና ለእግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ መኖር እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ የምንሆነው እኛው ነን፡፡

ሰው በእግዚአብሄር አምሳል እንደተፈጠረና ለእግዚአብሄር ክብር እንደተሰራ በህይወታችን የምናመለክተው እኛ ነን፡፡  እግዚአብሄርን ማክበር የሰው በምድር ላይ የመፈጠር አላማ መሆኑን የምናስታውሰው እኛ ነን፡፡ ምድርን ከሚታይ ነገርና ከስጋዊ ፍላጎት ከፍ ያለን ደረጃ የምንሰጣት እኛ የምድር ጨው ነን፡፡ በምድር ላይ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ስለመኖር ለሌሎች የምንመሰክረው እኛ ነን፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሄርንና ሰውን በመውደድ እንዴት እንደሚኖር የምንመሰክረው እኛ ነን፡፡

    ጨው ክብሩ ለምግብ ጣእም መስጠቱ ነው፡፡ የጨው ክብሩ ኮስታራነቱ ነው፡፡ እኛ ነን አለምን ማጣፈጥ የምንችለው፡፡ አለምን ለማጣፈጥ ጣእሙ ያለን እኛ ነን፡፡ እኛ ግን ይህንን ወሳኝ ሃላፊነታችንን ካልተወጣን ማንም ሊሰራልን አይችልም፡፡ እኛ አለምን ካላጣፈጥን እኛን ሊያጣፍጠን የሚችል አለም የለም፡፡ ጨው ደግሞ ካላጣፈጠ ለምንም አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ ነው ጨው በአለም ሁሉ መበተን ያለበት፡፡ ጨው በጨው እቃ ውስጥ ቢቀመጥ ምንም እንደማይጠቅም ሁሉ እኛም በየሰንበቱ መሰባሰባችንና ክርስትና ክርስትና ማለታችን ለሌላው ካልጠቀመ በጨለማው ላይ ካላበራና ለመራራው አለም ጣዕም ካልሰጠ ጠቃሚነቱ የማይታየው፡፡ ጨው ግን በተለያየ አይነት ወጥ ውስጥ ቢጨመር ያጣፍጣል ምግብ በሰሃን ተቀምጦ አጠገቡ በጠርሙስ ጨው መቀመጡ ምግቡን ሊያጣፍጠው እንደማይችል ነገር ግን  ከጠርሙሱ ውስጥ ወጥቶ ሊበተን እና ሊነሰሰነስ ይገባዋል ፡፡ ስለዚህ ክርስትያኖች የምንሰበሰበው ለመበረታታት ፣ ለመሞረድ ፣ ለመታደስ እና ለስራ ዝግጁ ሆነን ለመበተን ነው፡፡ ስራው በምድር ፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ነው፡፡ ጨውነታችን በትምህርት ቤት ፣ በሆስፒታል ፣ በእርሻ ፣ በሃገር አስተዳደር ፣ በውትድር ፣ በንግድና በመሳሰሉት ሙያዎችን ሁሉ ይፈለጋል፡፡

"እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። " ማቴዎስ 5፡13

ክርስትናን ካለራስ ወዳድነት በፍቅር ለሌሎች መልካም ምሳሌ በመሆን ክርስትናን እንዲቀበሉ የምናበረታታው የምድር ጨው በመሆን ነው፡፡

Kassu Boston 

bottom of page