top of page

ጌታ ኢየሱስ  ክርስቶስ  በክብር 

ተመልሶ ይመጣል !

   በዚህ ባለንበት ዘመን ከጥቂት ጸሎት ቤቶች በስተቀር ከብዙሃን ጸሎት ቤቶች መድረክ የጠፋው አና ርዕሱ እንኳን በስብከት መልክ እንዲዘጋጅ በአገልጋዮች ልብ አና በአጀንዳቸው ያልተዳሰሰ ነገር ቢኖር የጌታ ዳግም መመለስ (ምጽዓት) ጉዳይ ነው ። በአሁኑ ጊዜ ለተገባልን ዘላለማዊ ተስፋ ሳይሆን ለጊዜያዊ ጥቅማችን አና ለምድራዊ ኑሮ ፍላጎቶቻችን ብቻ ሆኗል ጌታን የምንጠራውና የምንጮኽው ። ነገር ግን የመንፈሱና የእውነተኛው ሙሽራይት ድምጽ ግን ለጊዜው በሆነ ነገር ላይ ሳይሆን ዘላለማዊው ተስፋ ላይ ያተኮረ ነው ።

   ጌታችንን ኢየሱስን የጠሩት መንፈሱና ሙሽራይቱ  ናቸው። ና ብለው የሚጠሩት የእግዚአብሄር መንፈስና ሙሽራይቱ ማለት ቤተክርስቲያን ናቸው ። እንግዲህ ና የሚለው ጥሪ አንባቢው እንዲያስተውል የሚያስፈልገው - አብሮ ለመሆን፤ በአንድ ነገር ውስጥ ስንሆን ለእርዳታየናፍቆት፤ ወዘተ .... ሊሆን ይችላል።

    ና የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ የምንጠቀመው በአካል ከእኛ ጥቂትም ይሁን ብዙ ሜትርና ኪሎሜትር (ማይልስ) የራቀውን ሰው ነው። እንግዲህ ይህን ጥሪ ያቀረቡት በምድር ላይ ያሉት መንፈሱና ሙሽራይቱ ቤተክርስቲያን ናቸው ። ለብዙዎቻችን ጥያቄ ውስጥ የሚከተን ነገር ቢኖር የመንፈስ ቅዱስ ና ብሎ መጥራት ነው ።

   አሁን ያለችው ቤተክርስቲያን(ሙሽራይቱ) ጌታን ምን አያለችው ይሆን የምትጠራው? ጌታ ኢየሱስን ቶሎ ና ማለት ትችላለች ? ወይስ ጌታ ሆይ አልተዘጋጀሁምና ትንሽ ቆይ እያለችው ይሆን? አንግዲህ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ አና ትኩረት ቤተክርስቲያን (ሙሽራይቱ) ከመንፈሱ ጋር አንድ አይነት ድምፅ እንድታሰማና አንድ አይነት ጥሪ እንድታደርግ ነው። ለዚህም ቤተክርስትያን ወደ ተጻፈላት ቃል መመለስ አለባት (ራእይ 19 ፡ 7-8)

  " ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና። የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ። ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና።"

    እዚህ ላይ ዮሐንስ የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ይለናል: በጉ ጌታ ኢየሱስ ነው ሰርጉ ደርሷል ይለናል:: ዝግጅቷ የሚስቱ (የሙሽራይቷ) ምን ይመስል ይሆን ? ምን ያህል ተዘጋጅታ ይሆን ? ዮሐንስ በራአይ ሲመለከት የተዘጋጀች ያጌጠችና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ የተጎናጸፈች ሙሽራ (ሚስት) አየ። ይህ የለበሰችው ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው ይለናል። ይህ ማለት የቤተክርስቲያን (የሙሽራይቱ) በትክክለኛ አቁዋም ላይ መገኘት ነው።

   ዝግጅት:- በትክክለኛ ሥራ አማኞች ሲገኙ ይህም በማቲ 5፡13-16 አንደሚናገረው ለአልጫው አና ጣአም ላጣው ዓለም ጨው: ለጨለማው ዓለም በመልካም ሥራ ብርሃን መሆንን ይጠይቃል። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ዛሬ ባሏ (ሙሽራው) ሲያያት ምን ዓይነት ልብስ ይሆን ለብሳ የምትታየው? አንባቢ ሆይ አናስተውል!

    ቤተክርስቲያን ስንል በሰው አጅ በባለሞያ የተሰራውን ባለ አራት ማእዘን ግንብ አጥር ጣራ የተከደነ ቤት ወይም ባማሩ መብራቶችና በተለያዩ ምስሎች ያሸበረቁ መሰብሰቢያ አዳራሾች ወይም በሃይማኖታዊ ወግና ስርዓት የተፈጠረውን ክርስቶስን የማያስገባ የደማስቆ መሰዊያ እያልን እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን።

   ዝግጅቱን የሚያደርጉት:- በክርስቶስ አምነው ምጽዓቱን የሚጠብቁት ቅዱሳን ይታጠቡ ዘንድ: ልብሳቸውን ይለውጡ ዘንድ: ይዋቡ ዘንድ: አንደ ሞአባዊቷ ሩት ወደ ቦዔዝ ለመሄድ ስትል በኖአሚን እንደተመከረች (ሩት 3 : 3) ዓይነት ዛሬም ሙሽራይቱ እንደታየላት ትሆን ዘንድና የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ በመስማት አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ እንድታደርግ ያስፈልጋታል። 

   (ኤፌሶን 5፡27) ባሏ ራሱን አሳልፎ የሰጠው ለምንድነው? ስንል እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ ለማቅረብ በመፈለግ ራሱን አሳልፎ ሰጠ ። ዛሬም ክርስቶስ ለምጽአቱ እንድንዘጋጅ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶናል:: ከእድፈት ከፊት መጨማደድ ከነውር ተለይተን በቅድስና እንጠብቀው ዘንድ ይፈልጋል::  

   

   (2ኛ ጴጥ 3 ፡ 12)  የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ይለናል::  አሜን ::

 

​ካሱ ከቦስተን 

bottom of page