top of page

 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ !

ይህ ገጽ በተለያዩ ርዕሶች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ለአንባብያን ያቀርባል: ከታች በተዘረዘሩት ርዕሶች ላይ ጽሁፎቻችሁን ፖስት ማድረግ ከፈለጋችሁ ይደውሉልን ወይም ይጻፉልን   
   
 
ወንጌል ያስፈራን ክርስቲያኖች 
 

   በዚህ ዘመን በምንኖር አማኞች የዕለት ተዕለት ኑሮና ግንኙነት ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ እሴቶች፣ እሳቤዎችና ምልክቶች ቀሰ በቀስ እየተሟጠጡና እየጠፉ ናቸው ።  አብዛኛዎቻችን መንፈሳዊ እርቃናችንን  የቀረን ክርስቲያኖች እየሆንን የመጣን ይመስላል ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊነት እንደ ኋላ ቀርነት እየታሰበ ነው። በቀድሞ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰው የሚከበረው በክርስቲያንነቱና በመንፈሳዊነቱ ነበር፤ አሁን ግን ዋጋ አሰጣጣችን እየተቀየረ በመምጣቱ፣ ለቤተ ክርስቲያን በሚሰጠው በአሥራት እና በፍቅር ስጦታ ገንዘብ፣ በእውቀቱ ወይም በትምህርት ደረጃው፣ በሙያውና በሀብቱ ሆኖል። አንድ ሰው ትርፍ የሚያስገኝልን እስካልሆነ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣቱም ሆነ መሄዱ አያስደንቀንም። እያንዳንዳችንም ሆነ፣ቤተ ክርስቲያን መንገዳችንን እየቀየስን ያለነው በመጽሓፍ ቅዱስ ዋጋ አሰጣጥ ሳይሆን፣ በዚህ ዓለም አሠራረና ስርዓት እየሆነ ነው።

     ዛሬ ዛሬ የስህተት ትምህርትና ሓሰተኛ ልምምዶች በየመድረኩ ላይ በሽ ናቸው። የውድቀታችን ብዛት የእምነታችንንና የትምህርታችን ዓይነትና ጥራት ያሳያል ቢባል ማጋነን አይሆንም። በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ጥርት ያለውና ትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ አይሰበክም። እርሱ ገሸሽ እየተደረገ በአዝናኝና አስቂኝ ተዋንያንና ትዕይንታቸው እየተተካ መጥቷል። ይህን ስናይ ቃሉ በቤቱ ነግሷል ለማለት አይቻልም። ጥንት ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ያሉ የአብያተ ክርስቲያናትን መድረክ ሌላ ትምህርት ተተክቷል እያልን እንነቅፋቸው ነበር ። አሁን ግን ወንጌላውያን ተብዬዎቹን መድረክ ሌላ ነገር ወረረው። ቃሉ በሌሎች ትምህርቶችና ልምምዶች ተተካ።

    ዛሬ የአሜሪካን ሕዝብ ሕይወት የሚመራው በአስር ሺ መጽሔቶች፣ በስድስት ሺ ሬድዮ ጣቢያዎች፣ ከአራት መቶ በላይ በሆኑ የቴሌቨዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች በየቀኑ በሚያቀርቡት ወሬ ነው። በከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠውን ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ዓለም ከሚገቡት አምስት መንፈሳዊ(ክርስቲያን) ሰዎች ውስጥ አራቱ የምድር ሕይወታቸውን የሚመሩበትን ትምህርት የሚያገኙት ከእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን፣ ከሚድያ ነው። በመሆኑም ዓለማዊነት የወንጌልን እውነት ከንግግራችንና ከውይይታችን መሐል እያገለለው ነው።

    በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች ስለ ፓለቲካ፣ ስለ እኩልነት፣ ለለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ ስፓርትና ፊልም አፋችን ተከፍቶ ስናወራ፣ በንግግራችን መሓል ግን ስለ እግዚአብሔርም ሆነ ስለ ወንጌል ማውራት እያሳፈረን መጥቷል። እንግዲህ ይህ ሁሉ ተግዳሮት ተጋርጦብናል።    

   በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የወንጌሉን ቃል ለዓለም በማድረስ የዚህን ዓለም እኩይ ዕለት ዕለት እያሸነፍን መሄድ የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ ሁሉ ክፉ አስተሳሰብና ተግባር እያንዳንዳችን በመዳን ቃሉ የሚፈልግብንን ሕይወት መኖር የምንችለው ምን ብናደርግ  ነው?  በምድር ላይ ያለችው የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በመላው አገሪቱ በመስፋፋት ትውልዱን በወንጌል ኃይል ተጽዕኖ ወደ እግዚአብሔር የመመለስ ጥሪ አለባት፤

 እያንዳንዳችን ምን ብናደርግ ነው ህዝብን ከጥፋት መንገድ ልንመልሰው የምንችለው?

የሰው ልጆችን ከታሰሩበት የኃጢአት፣ የዓለምና የሠይጣን እስራት ነፃ እያውጡ በሳል የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ማድረግ ይቻላል? እንዴት? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ጌታ ራሱ በልዩ ጉብኝት ወደ ምድራችንና ወደ ሕይወታችን መምጣት አለበት ( ልዩ መንፈሳዊ ተሓድሶና መነቃቃት ያስፈልገናል የምንለው ለዚህ ነው)ይህ እንዲሆን ደግሞ የጌታን መንገድ መጥረግና ማስተካከል ያስፈልገናል። ለፈጣን መለኮታዊ ጉብኝት የመንገድ ጠረጋውን ሥራ የሚሠሩ አገልጋዮችን እግዚአብሔር እንዲቀሰቅስልን ብንጸልይ መጎብኘታችንን እግዚአብሔር ያፈጥነዋል። ለወንጌሉ አገልግሎት የኋላ ደጀን የሚሆኑ፣እንዲሁም ምዕመናንን፣ በአጥቢያና በቤተ እምነት ደረጃ ያሉ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍሎችን በጸሎት የሚደግፉ በቂና ተዋጊ የጸሎት ቡድኖችን በማቋቋም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ ሠፊ የጸሎት ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ ያስገልጋል።

   የተዘጉ ቦታዎች እንዲከፈቱ የምንፈገልግ ከሆነ ፣ በቅጡ የተደራጀና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የታጠቀ (የተሞላ) የጸሎትሕይወት እጅግ አስፈላጊ ነው። ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ተሓድሶና መነቃቃት እንዲሆንልን የምንፈልግ ከሆነ የእግዚአብሔር ሀልዎት የሚገኝበት የጸሎት ሕይወት ያስፈልገናል።የጌታን መንገድ አዘጋጁ የሚለው የነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት በዚህም ዘመን ለምንኖር አማኞች መልእክት አለው። የጌታን መንገድ ስናዘጋጅ ጌታ ይመጣል።

                          አሜን ይሁንልን !!!

ካሱ ቦስተን 

 

መቅደሱ ይፈተሽ

. . . የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ (ዮሐ.2፣16)

 

   በኢየሩሳሌም ያለው ቤተመቅደስ የተሠራው እግዚአብሔር አምላክ እንዲመለክበት ነበር፤ ሆኖም የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ በነበረ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ወደዚያ ሲሄድ በቤተመቅደስ ውስጥ ያየው በጣም የሚያሳዝን ነገር ነበር፡፡ በመቅደስ በሬዎች በጎች ርግቦች ይሸጡ ነበር የገንዘብ ለዋጮችም ተቀምጠው ነበር፡፡ ይህንን ያየው ጌታ የቤቱ ቅናት በላው እናም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉንም በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፤ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡

  ምናልባት እነዚህ ሠዎች ለመስዋዕት የሚሆን ነገር ያዘጋጁ ይመስላል አላማቸው ግን ንግድ ነበር፡፡ ግራ ተጋብተዋል መገለጡ ጠፍቶባቸዋል የሚሠሩትን ስራ፣ የተለማመዱትን ልምምድ፣ ትክክል ነው ብለው ወስነዋል ጎብኚው እስኪመጣና ጅራፍ እስኪያነሳ ተስማምቶአቸዋል፡፡ ሥራቸው ሁሉ ቤተመቅደሱ ከተሠራበት አላማ ጋር የተቃረነ ነበር፤ ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ያላቸው፡፡

  ዛሬ ቤተ መቅደስ የሆነው ሠውነታችን በምንድነው የተሞላው? የቤተመቅደሱ ባለቤት ለፍተሻ ሲመጣ ምን ይመለከት ይሆን? በዚህ ሠውነታችን ጌታን ልናከብር ተጠርተን ሣለ ልክ በዛ ዘመን እንደነበረው ሕዝብ አላማችንን ዘንግተን ወጣ ብለን ይሆን? የቅዱሣን መሠብሠብ አላማው ምን ይሆን? በስብሠባችን ጌታን እያከበርነው ነው ወይስ ንግዱን እያጧጧፍን ይሆን? ጌታ ኢየሱስ ወደ መቅደሳችን ሲመጣ ይደሰታል? በእውነት በዚህ ዘመን መንገዳችንን እንመርምር ሕይወታችንንና ስብሰባችንን እንይ፡፡  

  አላማችን በግል ሕይወታችንም ሆነ በመሰባሰባችን ጌታን ለማክበር እርሱን ለማምለክ ይሁን፡፡ ስለዚህ መቅደሱ ይፈተሽ እያልኩ ነው፡፡ አሜን ይፈተሽ !!!

​ካሱ ቦስትን 

ጋብቻ 

መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።

(ወደ ዕብራውያን 13፥4)

  

    በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ጋብቻን በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን ነው ያለው በሁሉ ዘንድ ሲል በሴቷም በወንዱም በእስልምናውም በክርስትናውም በማንኛውም የሰው ዘር ሊከበር ይገባዋል ነው የሚለው እንዲሁ እንደቀልድ የሚታይ ነገር አይደለም እንደቀልድ ዛሬ ተገብቶበት ነገ የሚወጣበት እንደዘበት የሚታይ ጉዳይ አይደለም ነው የሚለን ።

  ሌላው ደግሞ ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል (የተሰመረበት ሃሳብ ሊተኮርበት የሚገባው ነው) የሚፈጸም የመንፈስ የነፍስ እና የስጋ ጥምረት ያለበት ነው ይህም ጋብቻ በሁለት ተቃራኒ ጾታ መሃከል የሚፈጸም እና ዘለቄታ ያለው በእግዚአብሔር በቅዱሳን መላአክቱና እና  በሰው ፊት የሚደረግ የቃልኪዳን ትስስር ያለበት ስርዓት ነው ።   

  ዛሬ ዛሬ እንደምናየው ግን የጋብቻን ክቡርነት በዘነጉና ጋብቻ እንዴት እንደተጀመረ ባልተረዱ ግለሰቦችና የጋብቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች እንዲሁም የሃይማኖት ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸመው ቅጥ ያጣ እና ስርዓት የሌለው ወንድና ወንድን እንዲሁም ሴትና ሴትን እያጣመሩ ጋብቻን የመሰረቱ የሚመስላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በምድር ላይ ጥፋትን እንጂ መልካም የሆነን ስርዓት እየፈጽሙ ላለመሆናቸው ሊረዱት ይገባቸዋል። እነዚህን ግለሰቦች ደግሞ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላልና   ( ... ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 1 ቆሮ 6 : 9-10)

ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ከፈረደባቸው ስርዓቱን እያስፈጸሙ ያሉትም ከዚህ ፍርድ የሚያመልጡበት መንገድ አይታየንም ስለዚህ ይህንን ስርዓት ከማስፈጸም ሊታቀቡ ይገባቸዋል አንላለን።

   ከዚህ የባሰው የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት ደግሞ ይህንን ስርዓት መንግስት ስለፈቀደውና በሕግ ስለተደገፈ ብቻ እግዚአብሔር የፈቀደው ያህል በእግዚአብሔር እናምናለን የሚሉና እግዚአብሔርን እናገለግላለን የሚሉ ግለሰቦችና የሃይማኖት ድርጅቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን ያለማሰማታችውና ዝም የማለታቸው ጉዳይ ስርዓቱን ተስማምተው መቀበላቸውን የሚያሳይ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን እንደማይችል እንገነዘባለን። ትንሽ ቆይቶም እነዚሁ ግለሰቦች ስርዓቱን ለመፈጸም ወይም ጋብቻን ለመፈጸም ወደቤተክርስቲያን ቢመጡ የሚሰጣቸው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለብንም ምክንያቱም አስቀድመን የተቃውሞ ድምጻችንን አላሰማንምና ።

   ይህንን ስርዓት እያስፈጸሙ ያሉና ለማስፈጸም ችግር እንደሌለበትና የማያስጠይቃቸው የመሰላቸው ቤተአምልኮዎች ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከአባታቸው ከዲያብሎስ ዘነድ የተላኩ የጥፋት መልእክተኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም ።

     ስለዚህ በማስጠንቀቅም ይህንን ልንላችሁ እንወዳለን ራሳችሁን ብትመረምሩና ከየት እንደወደቃችሁ ብታስቡና ንስሐ ብትገቡ የትሻለ ነው እንላለን። በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦ ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ። ዳሩ ግን፦ ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም። እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። (ራእይ 2:18 - 23)

ካሱ ቦስተን 

ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?

 

. . . ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፡፡ . . . (ዮሐ.13፣13-14)

የሠዎችን ልጆች በማዳን አዲስ ምዕራፍ አዲስ ኪዳን የከፈተው ጌታ ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፣ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው፡፡ ለብዙ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን በተለያዩ መንገዶች አስተምሯል አንዳንዴ በቃል በምሳሌ በተግባር ዛሬ ደግሞ በዚህ ክፍል ፍቅርን በተግባር ሲያስተምራቸው እንመለከታለን፡፡

  በዚህ ክፍል ያደረገው ነገር ደቀመዛሙርቱን አስደንግጦአቸዋል ምክንያቱም እግር ማጠብ ዝቅ ማለትን ያመለክታል በተለይም አንድ መምህር ተማሪዎቹን ጌታ አገልጋዮቹን ዝቅ ብሎ እግር ማጠብ የማይታሰብ ነው፡፡ ሌላውን የአካል ክፍል ቢሆን ችግር የለውም ነበር ጌታ ኢየሱስ ግን ተነስቶ እግራቸውን አጠበ በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ አበሠ በጣም የሚገርም ነው፤ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ ቀደም እንዲህ ሲደረግ ሠምተውም አይተውም አያውቁም፤ ምናልባትም መምህር የሚባሉት ጌታ የሚባሉት የከበሬታ ወንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው እግር ሲያሳጥቡ ነው የሚያውቁት ዛሬ ግን የተገላቢጦሽ ሆነባቸው፡፡ ለዚህ ነው ስምዖን ጴጥሮስ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም ያለው፡፡

  ጌታ ሆኖ መምህር ሆኖላቸው ዝቅ ብሎ እግራቸውን አጠበ፡፡ እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ከተቀመጠ በኋላ አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? አዎን መምህር ነኝ ደግሞም ጌታ ነኝ እንዲህ ሆኖ ሳለ እኔ ይህንን ካደረኩላችሁ በተግባር ካሳየኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ልትተጣጠቡ ይገባል አላቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሠዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ፍቅር እራሱን ዝቅ በማድረግ በተግባር ገለፀ፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፡፡

  የዘመናችን አገልጋዮች ቄሶች፣ መምህራን፣ ነቢያት፣ ፓስተሮች፣ ሃዋርያት እንዲሁም ሽማግሌዎች . . . እስቲ እንደ ጌታችን እንዳስተማረንም ወርደን የደቀመዛሙርቱን እግር እንጠብ ፍቅርንም ለሕዝብ በተግባር እናሳይ የከበሬታ ወንበርን አንፈልግ፡፡

  ወዳጄ ዛሬ ይህ ምሳሌ የተሠጠን ፍቅራችንንና ትህትናችንን ዝቅ እስከ ማለት ድረስ እንድንገልፅ እንጂ በየቤቱ እየሄድን የሠዎችን እግር እንድናጥብ አይደለም ነገር ግን በፍቅርና በትህትና ተገቢ እስካማይሆንበት ድረስ እንኳ ሠዎችን በትህትና ይቅር እንድንል እንድንወድድ ነው፡፡

 ጌታ ኢየሱስ እኔ እንደወደድኋሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ አለ፡፡ እንዲሁም እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያወቃሉ አለ፡፡(ዮሃ 13:34)

 ወዳጄ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነህን? ትህትና በተሞላበት ሕይወት ባልንጀራህን ውደደው እግር እስከ ማጠብ ድረስ እስከ መጨረሻ ውደደው፡፡ እኔ እንደወደድኋችሁ ነው ያለው ጌታ ኢየሱስ፡፡ ለመሆኑ የተወደድክበትን ፍቅር ጥልቀት ታውቀዋለህን? ከአእምሮ በላይ ነው ፍፁም፣ ጥልቅ እውነተኛ በሆነ ፍቅር ተወድደሃል የኢየሱስን ፍቅር ልትገልፀው ትችላለህን? ቆሻሻህን ጉድህን ሸፍኖ በአደባባይ ሳያወጣ በደሙ አጥቦልሃል ያለፈውን ጉድፍ ከሰው ፊት የማያቀርበውን ሃጢዓትህን ይቅር ብሎልሃል ዳግመኛ ላያስበውም ቃል ገብቶልሃል ፍቅሩን ትዘነጋለህ? ታዲያ እርሱ እንዲህ ከወደደህ ጉድህን በአደባባይ ሳያወጣ ይቅር ካለህ ለምን የባልነጀራህን ጉድ ታወጣለህ? ለምን ስለ ባልንጀራህ ቆሻሻ ታወራለህ? ዓመት ሁለት ዓመት ዓምስት ዓመት የቆየ ቁርሾ እየነቀስክ ለምን ታወራለህ፡፡ ይቅር የተባልክበትን ታላቅ ፍቅር አስብ እንደዛው ጌታ እንደ ወደደህ ባልንጀራህን ውደድ ይቅር በለው፡፡ ይህ ፍቅር በመካከላችን በእውነት ይኑር፡፡

በጩኸታችንና በዝማሬያችን ብዛት ሳይሆን በፍቅራችን ብዛት በእውነት የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆናችንን ሰዎች ሁሉ ይወቁ፡፡

              ተባረኩልኝ፡፡

                                               ካሱ ቦስተን

ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ​!

 "የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን  ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ  ታላቅ ዕልልታ አደረጉ ምድሪቱም አስተጋባች። ፍልስጥኤማውያንም የዕልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ  ታላቅ የዕልልታ ድምፅ ምንድን ነው?አሉ" (1ሣሙ. 4፥5-6) እስራኤል ብዙ ዕልልታ ባደረጉ ጊዜ ምድሪቱ አስተጋባች ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ ተሸንፈዋል በፍልስጥኤማውያን ፊት ድል ተመትተዋል። መሸነፋቸው  ታቦቱን ይዘው ስላልወጡና በብዙ ዕልልታ ስላላመለኩ ስለመሰላቸው ታቦቱን ይዘው ወጡ በብዙ ዕልልታም ምድሪቱ አስተጋባች። የሚያሳዝነው ግን ይህን ሁሉ አድርገውም ከመሸነፍ አልዳኑም ታቦቱም ተማረከ።

   ታሪክ ራሱን ይደግማል ማለት ይህ ነው ወዳጆች ሆይ ዛሬም ሣናስተውል ታሪክን እየደገምን ነው? በብዙ ጠብና ክርክር እየኖርን በአዋጅና በመግለጫ ጌታ የሞተለትን ወዲያ አሽቀንጥረን ጥለን አባረን የይቅርታ ልብ ሳይኖረን እንደውም ለይቅርታ በራችንን ቆልፈን በፍቅርና በአንድነት በህብረት የጌታን የወንጌል ጥሪ ላልዳኑት ለማዳረስ ፈቃዳችንን ሳንሰጥ እነዲሁ በራሳችን ጉዳይ ተጠምደን እንከርምና በሳምንት አንድ ቀን መንፈሳዊ ለመምሰል ደፋ ቀና ስንል ይባስ ብለን የጌታ ራት ስርዓትን ለመፈፀምና ለማስፈፀም ተፍ ተፍ ስንል ( እንዲያውም ለጌታ ራት ማስታወቂያ በወንድሙ ላይ ቂም የያዘ እንዳይወስድ ብለን እንናገራለን ማስታወቂያው ሰጪውን ቄስ ፓስተር ወይም ሽማግሌ ስርዓቱን ለማስፈፀም የሚቆመውን አይከለክል ይሆን ?)

ይህን ሁሉ ድርጊታችንን በዙፋኑ ላይ ያለው ጌታ ምን ይል ይሆን?ጌታ የሌለበት የጌታ ራት!አይገርምም!

   ኧረ እንደውም መንፈሳዊ ድርቀት ያጠቃን ሲመስለን ለሰልፍ እንወጣለን ኮንፈረንሱ ይዘጋጃል፣ ብዙ ጩኸትና ዕልልታ ይደረጋል ምድሪቱ ታስተጋባለች ድል ግን የለም። በአንድ አጋንንት ፊት ውጣ እየተባለ ሃያ አራት ሰዓት ይጮሃል ድል ግን የለም። ስማችን በአህዛብ ዘንድ መዘበቻ ሆኖአል።

  ለምን? የሚል በመንፈስ የደፈረ ጠያቂ ቢኖር መልሱ እግዚአብሔር በቤቱ አልተከበረም፣ በእውነት አልተመለከም፣ በእውነትና በመንፈስ ማምለክ ማለት እንደሚገባን በከበሮና በልልታ መጮህና ማስጮህ አይደለም። በዚህ ዘመን እኛ በጩኸትና ሰፈር በመረበሽ ሃይለኞች ነን ላባችን ጠብ እስኪል ድረስ የእግዚአብሄር ኃይል ግን የለም፣ ምድሪቱ በዕልልታችንና በዝማሬአችንና በመጮሃችን ብታስተጋባም እግዚአብሔር ግን በዚያ ውስጥ የለም። ዝማሬአችንና ጩኸታችን ቅድስናን አይተካምና በቅድስና በቤቱ ካልኖርን በወንድማማች ፍቅር ካልተመላለስን ኃይሉ አይገለጥም። ጌታ የሞተለትን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነውን ቤተመቅደሱን እያፈረስን እንዲሁ ማገልገላችን በእኛም በዓለምም ትዝብት ውስጥ ይከተናልና። በተለይ ይህንን መልእክት ቤተክርስቲያንን የአገልግሎት ክፍሎችን እንዲሁም ጉባኤዎችን እየመራችሁ ላላችሁት አገልግሎታችሁን እንድትመረምሩት አጠንክሬ አሳስባችኋለሁ።

የእግዚአብሄር ቃል “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ”  እንደሚል በውስጣችሁ ያለውን ሳያውቁ ለጌታ ብለው ለተከተሉዋችሁ ለመንጋዎቻችሁ ልትጠነቀቁለት ይገባል እላለሁ።  

የአምልኮ ቤታችን ቢያምር ወንበራችን ቢመች ፀሎት ቤታችን በብዙ የከበሩ በተባሉ ቁሳቁሶች ቢሞላ ጌታ  ከሌለ ከንቱ ነው።

ጌታን ይዘን እንጂ ፀሎት ቤት ታቅፈን ህይወት አይሆንልንም።

 

                         ካሱ ቦስተን

 

ግዜው ተቃርቧልና ተዋደዱ !

ቤተክርስቲያን ሆይ አስተውይ !!!

መንፈስ ለአብያተክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ !!!

 

  ሰላም ቅዱሳን ለመሆን የተጠራን ወገኖች እንዴት ናችሁ? ዛሬም በተለመደውና ወስጤ በሚጮህ የቅዱሳን ፍቅር እጦት ላይ ያለኝን ሃሳብ በፍቅር ብዕሬ አስፍሬ ብቅ ብያለሁና ሳትሰለቹ  ማንበባችሁን ቀጥሉ።

  የእግዚአብሄር ቃል ሲናገር በዮሃንስ 13፡35 ላይ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ ይላል ። ቤተክርስቲያን ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት አመታቶች ውስጥ እየታወቀችበት ያለችውና በዓለም ዘንድ እንኳን ሳይቀር የተገለጠችበት መለያዋ አንዱ የፍቅር ማጣት ሂደት ነው ቢባል ሃሰት አይባልም ምክኒያቱም ምካሰሳችንና መነካከሳችን ከቤተክርስቲያን አልፎ የዓለምን የፍትህ አካላቶች እንድንፈልግ ካደረገን ዋል አደር ብሏልና።  

   እኛ በክርስቶስ ደም የተዋጀን የክርስቶስ አማኞች መታወቂያችን ሊሆን የሚገባው አንዱና ዋነኛው ፍቅር ነው ይህም ጌታ ከሰጠን መመሪያ አንዱና ብቸኛው እንዲሁም የመጀመሪያው ትዕዛዝ ነበር ትዕዛዙም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንድናምንና እርሱ እንዳዘዘንም እርስበርሳችን እንድንዋደድ ነው።(1ኛ ዮሃ 3፣23)  ሆኖም ግን ይህ ሊሆን አልተቻለም። አሁን ግን ያለንበትን ወይም የቆምንበትን ተገንዝበን ከገባንበት አዘቅት ውስጥ የምንወጣበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል። ከእንቅልፍ የምንነሳበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን ልናውቅና፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅም መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ እንደቀረበ ልናስተውል ይገባል።

  ወገኖች እግዚአብሄር በስራ ላይ ነው። በልጆቹ ያጣውን ሊያየው የሚፈልገውን ፍቅር በተገላቢጦሽ ዓለም እየተገበረችው መሆኗን ብናስተውል መተኛት ባልተገባን ነበር። በምድራችን ኢትዮጵያ እግዚአብሄር እያደረገ ያለው በቤቱ ያለን ልጆቹ ለፍቅር እጃችንን መዘርጋት ሲያቅተን እኛን ለማሳፈርና እንድናስተውል ሊያደርግ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል። ለዘመናት ደም ሲፈስባት የነበረች ምድር ወንድማማቾችን ያለያየ ድንበርና ግድብ ሰርቶ የተቀመጠ ቂም እንዲህ በአንድ ጊዜ ሲፈርስ፤ ሰዎች ሁሉ ድንበሩን አፍርሰው፤ የትናንቱን በደልና ቂም አራግፈው ጥለው፤ መሪዎቹም ትናንት በህዝቤ ላይ በደልና ግፍ ፈጽመሃልና መጥተህ በህዝቡ ፊት ይቅርታ ጠይቅ (ንስሃ ግባ) ሳይባባሉ፤ ፍቅር በደልን አይቆጥርም በደልን ይሸፍናል ተባብለው እጃቸውን ለፍቅር ሲዘረጉና ራሳቸውን ሲሰጡ ስናይ እኛ ክርስቲያኖች ምን ይሰማን ይሆን ??? እግዚአብሄር እናንተም እንደዚሁ አድርጉ እያለን ቃላት ባልበዛበት በተግባር በማሳየት እያስተማረን እንደሆን አላስተዋልን ይሆን ?? መንፈስ ለአብያተክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ !!!

  ስለፍቅር ለዘመናት ስንሰብክ ቆይተናል፤ እንደውም ዋናውና የተለየው ፍቅር ነው እያልን አስተምረናል ተምረናል፤ ዘምረናል አስዘምረናል፣ ነገር ግን የበደሉንን ይቅር ማለት ተስኖን ያለፈና የተረሳ፣ ያረጀ ቂምና ቁርሾ ይዘን እርሱኑ እያነሳን አትድረስብኝ አልደርስብህም በመባባል ክልልና ድንበር ሰርተን ተቀምጠናል።

  ይህን ጽሁፍ የምታነቡ ቅዱሳን ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያላችሁበት ሆናችሁ እ/ር በአገራችን ላይ እየሰራ ያለውን ድንበር፤ ቂም፤ ጥላቻን ያፈረሰ ፍቅር አድንቀን ዛሬም ለእ/ር የሚሳነው የለም በማለት ይህንን የመሰለ ራዕይና ጥማትን ይዘን ወደቤተክርስቲያን ዘወር እንበል እላለሁ። ዛሬ በአንድ ከተማ ውስጥ የእኔ፤ የእኛ፤ የእከሌ ቤተክርስቲያን ከመባባልና ጥላቻንና ቂምን ትተን ድንበርን በሚያፈርስ በጌታ ፍቅር አንድ በመሆን የጌታን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስና በፍቅር ለመገለጥ እንድንችል እጅ ለእጅ እንያያዝ እላለሁ። ዛሬ ከቃላት ባለፈ በተግባር ልንገለጥ ይገባል። ጌታ የጥልን ግድግዳ አፍርሶታልና፤ የፈረሰውን ግድግዳ እኛ ልንገነባ አይገባንምና፤ የቂም፤ የጥላቻ፤ የበቀል ግድግዳን አፈራርሰን ጌታን ለማስከበር አንድ ለመሆን ቃል እንግባ። እንነሳ ! እንነሳ ! እንነሳ !

      እኔና ቤቴ ይህንን ናፍቀን ተነስተናል እናንተስ ???                       

 

ካሱ ቦስተን

የክርስቶስ ክቡር ደም

 


 

"ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ" (1ጴጥ 1፡19)

  • ዛሬ ላይ ቆመን በእምነት ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት በቀራኒዮ መስቀል ላይ ወደ ፈሰሰው “ክቡር ደም” ስንመለከት፣ በምስማር ከተቸነከሩት እጆቹና እግሮቹ፣ እንዲሁም በጦር ከተወጋው ጎኑ፣ በእሾኽ ከተበሳው አናቱና ግብባሩ በአጠቃላይ ከበዛ ግርፋቱና ከቆሰለው አካሉ የሚጎርፋውን ክቡር ደም እናያለን። ያ ደም በመስቀል ላይ ፈጽሞ ተንጠፍጥፎ የፈሰሰ ደም፤ የንጹህ ሰው ደግሞም የእግዚአብሔር ደም ነው (ሐዋ 20፡28) ። በውስጡ ካለው የቤዛነትና ዓለምን የማስታረቅ ሥራ ኅጢአትን ለዘላለም የማስተሠረይ ብቃት አለው። ስለዚህ በእርሱ ለሚያምኑቱ ሁሉ በምንም የማይለውጥ በጸጋ የሆነ ፣በእምነት ብቻ ጸንቶ የሚገኝና የሚቆም ድነትን አስገኝቷል። በስሙ በማመን የልጅነትን ሥልጣን የተቀበለው የእግዚአብሔር ሕዝብ በደሉና መተላለፉ፣ ከሕግ እርግማንና ፍርድ ነፃ የሚያወጣው ጽድቅ የታወጀለት፣ እንዲሁም ከከንቱ ኑሮ በመ1,ላቀቅ አርነት በመውጣት በነፃነት የሚኖርበትን ሕይወት ያገኘው በዚሁ ክቡር ደም ነው( 1ጴጥ 1፣ 18)። ይህም ብቻ ዓይደለም ይህ ሕዝብ በዚሁ ውድ ደም ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ተመስርቶለት ሰምያዊ ዜግነትን አግኝቷል።

 

      ኢየሱስ በሞቱ ጊዜ በምጥ እናጣጣረና የሰቆቃ ጩኸት እያሰማ ስለ ዘላለማዊ የኅጢአት ሥርየትና ይቅርታ ደሙን በቀራኒዮ መስቀል ላይ ጨርሶ አንጠፍጥፎ አፍስሶታል። ከዚህ ከፈሰሰው የኪዳን ደም የተነሳ የማይቻለው የኃጢአተኛ ሰው መዳን የሚቻል ሆነ። ክብር ለኢየሱስ ይሁን ።     

 

  • የክርስቶስ ደም ከማንጻት ኅይሉና ብቃቱ የተነሳ፣ ከኅጢአት ሁሉ መንፃትን አስገኝቷል ። ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ እዚህ ደም ሲናገር፣ "ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል" በማለት በመልዕክቱ ውስጥ የወንጌልን 0m ይነግረናል (1ዮሐ 1፡7)። ነቢዩ ኢሳይያስም "ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች" በማለት ፍጹሙን የኅጢአት ይቅርታ ተስፋ ያንጸባርቃል (ኢሳ 1፡18)። ይህ የመንጻት ተስፋ ያለ ኢየሰስ ደም የሚታሰብ አይደለም። ኅጢአተኛ በክርስቶስ በማመን በእግዚአብሔር ፊት በእምነት ጽድቅ ሲቆጠርለት፣ ከክርስቶስ ደም የተነሳ አማኙ ላይ የቀረችና የምትታይ አንዲት ጥቁር ነጥብ ወይም የኃጢአት ርዝራዥ አትኖርም። ገና የቀረ የፊት መጨማደድም ሆነ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይገኝም።

   

     በእግዚአብሔር ፊት እንደ ደምም የቀላው የሰው ልጅ ኃጢአት እንደ ባዘቶ የሚያነጻው ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት በእለት ዓርብ በቀራኒዩ መስቀል ላይ በፈሰሰው በኢየሱስ ክቡር ደም ብቻ ነው። ዮሐንስ በራዕዩ “ ልብሳቸውን በበጉ ደም የሚያነጹ ብጹዓን ናቸው” ይላል። ልብስ መንፈሳዊ ማንነትን የሚያሳይ ዘይቤያዊ ንግግር ነው። የሰው ከኅጢአተኝነት ሕይወት ሊነፃ ፣ ሊታጠብና ሊቀደስ የሚችለው በበጎ ጥረቱና በሰብዓዊ ድካሙ ሳይሆን፣ በደሙ ብቻ ልብሳችን/ ሕወታችን ይነጻል (ራዕ 7፡14)። ደም የነካው ልብስ መቆሸሹ እሙን ነው፣ ውድና ክቡር የሆነውን የኢየሱስን ደም የተረጨ ልብስ ግን እንደ አመዳይ መንጻቱ፣ እንደ ባዘቶም መጥራቱ ተአምር ነው።

 

  • ደሙ ያነጻው ለዘላለም ነጽቶአል። ንጹህ ያደረገን ክቡር የሆነው ደሙ፣ እጅግ የበዛውን የሰው ልጅ ኅጢአት አስወግዷል፣ ያስወግዳልም። ይህ ደም የሰውን የኅጢአት ዝገት አስወግዶ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ካመጸበት ከብዙ ዓይነት መንገድ እየመለሰ በውድ ልጁ በኩል በአብ ፊት እንዲቀርብ ያስችለዋል (ኤፌ 1፡6)። ከዚህ ውጭ ጊዜ እየጠበቁ የሚካሄዱ ኅይማኖታዊ ሥርዐቶች ለኅጢአተኛው የሰው ልጅ ዘላለማዊ የኅጢአትን ይቅርታና የበደልን ሥርየት አያስገኙለም። ጸሎት መልካም ነው ፤ ክርስቶስ ደሙን ካፈሰሰበት ዓላማ ውጭ ከሆነ ግን የሰው ድካም ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት በጸጋ የሰጠውን ሰው በመልካም ግብሩ ለመጨበት ወደ ሰማይ ቢዘረጋ ሊያገኘው አይችልም። እንዲህ ከሆነ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ፣ በከንቱም ደሙን አፈሰሰ።

  

      የክርስቶስ ደም በያዘው ኃይል ምክንያት ውድና ክቡር ደም ነው። ከመርጨቱ ደም በታች እስካለን ድረስ ከአጥፊው መልዓክ መቅሰፍት መጠበቃችን አስተማማኝ ነው። እስከ ዛሬ ሕይወታችን የመቆየቱ፣ ነፍሳችንንም ለዘላለም ሕይወት የመስንበትዋ ምሥጥርና እውነተኛ ምክንያት እግዚአብሔር ደሙን ስላየ ብቻ ነው። እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል ለማክበር በተዘጋጁበት ጊዜ "ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንት አልፋለሁ"። ብሏቸዋል እግዚአብሔር ወደ ቤታችን እንዲሁም ወደ ህይወታችን ሲያይ የሚታየው የልጁ ክቡር ደም ነው። እኛ ዐይኖቻችን ሲፈዙና ከማየት ሲደክሙ፣ የእግዚአብሔር ዐይኖች ግን አሁንም ደሙን ለማየት ያው ብሩህ ናቸው፣ አይደክሙም፤ ይህም ታላቅ መጽናናት ነው።

 

  • የክርስቶስ ደም የሚቀድስ ከመሆኑ የተነሳ፣ አሁንም እንደገና ክቡር ነው። ኃጢአታችንን በማስወገድ ያጸደቀን ያው ክቡር ደም መልሶ ደግሞ አዲሱን ሰው በመቀስቀስ ኃጢአትን በማሸነፍና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመፈጸም እንዲኖር አበርትቶ ወደ ፊት ያስኬደዋል። ክቡሩ ደም ደካማውን ሰው ያበረታዋል። ለቅድስና ህይወት መነሳሳትም ሆነ ለጽድቅ ኑሮ ከኢየሱስ ደም ሥሮች ከሚፈሰው ክቡር ደም በላይ የላቀ ቀስቃሽ ኃይል ከቶ የለም።

 

  • ደሙ ውድና ክቡር ነው፣ በቃላትም ሊገለጥ ከሚቻለው በላይ ክቡር ደም ነው፣ ምክንያቱም ድል የመንሳት ኃይል አለው፤ "...ከበጉም ደም የተነሳ ድል ነሱ" (ራዕ 12፡11) ተብሎ ተጽፎአልና። ከደሙ በቀር በዲያብሎስ ላይ ድልን የሚያቀዳጅ ሌላ ምን ነገር አለ? ክቡር በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ሰልፍ የሚያደርግ ሰው ሊሸነፍ በማይችልና ሽንፈትን በማያውቅ የጦር እቃ የሚዋጋ ሰው ነው። ዲያብሎስም በዚህ እቃ ጦራችንና ክቡር በሆነው የኢየሱስ ደም አንጻር ጥቃትን ሊከላከል የሚያስችለው ምንም መስረት የለውም።

 

በጌታ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች “ደስ ይበላችሁ” በርቱና ተዋጉ ከኢየሱስ ክቡር ደም የተነሳ ዲያብሎስ መከላከያ የለውም። ማጥቃትም ሆነ ድል መንሳት የእናንተ ነው። ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት በቀራኒዮ ላይ በፈሰሰው በኢየሱስ ደም፣ ኃጢአት ጉልበቱን ያጣል፣ ሞትም ሞት መሆኑን ያቆማል፣ መቃብርም ሙታኑን አይከለክልም፣ የገሃነምም ደጆች ይሰበራሉ፣ የሰማያትም ደጆች ይከፈታሉ፣ ነፍሳትም ከሲኦል ያመልጣሉ። የኢየሱስ ደም በክቡርነቱ በያዘውና በተሞላው ኃይል፣ በጉልበቱና በአቅሙ ከታመንን፣ በእርሱ ድል እየነሳን ድል በድል እንሄዳለን።

 ካሱ ቦስተን

የታረደው በግ ባለጠግነትና ክብር ይገባዋል!!

መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ ! 

1ኛ ጴጥሮስ 2፡5

ክፍል 1.

   በመንፈሳዊ ሕይወት እያደግን ስንሄድ የደስታችን ምንጭ ምን መሆኑን እንገነዘባለን። መሰረታዊ እውነቶችን በአግባቡ እየተረዳን ስንመጣ ሙሉ በሙሉ ልንገልጸው የማንችለውን የዘለዓለም ሕይወት፣ ደስታና ሰላም የሰጠንን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንናፍቃለን። ከነዚህ መሰረታዊ እውነቶች መካከል አንዱ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኙ ሁሉ የክርስቶስ አካል የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ብልቶች መሆናቸው ነው።

አዲስ ኪዳን ስለዚህ ሲናገር፤ “እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ” ይላል (1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12:27) ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆና እንድትገኝ ለክርስቶስ ታጭታለች። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን እንደዚህ ይገልጸዋል፤ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፣ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፣” 2ኛ ቆሮ 11፡2

   ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በላከው መልእክት ደግሞ፡ “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት፣ ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ይላል (ኤፌሶን 5፡27)።

     ልዑል እግዚአብሔር በክቡር ልጁ ደም የዋጃት የቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቶስ አካል፣ ብልቶች ከሆንን እና ጌታ አምላክ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት፣ ንጽህት እና ነውር የሌለባት እንድትሆን ካዘዘ፤ እኛም እያንዳንዳችን በቃሉና በመንፈሱ በመታጠብ ልንቀደስና ለእርሱም ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ልንሰራ ያስፈልጋል።

     ዛሬ በአዲስ ኪዳን ዘመን ያለን ክርስቲያኖችም እንዲሁ በገዛ ራሱ ደም የዋጀንን እና የዘለዓለምን ሕይወት የሰጠንን ጌታ የምናመልከው በቤተ ክርስቲያንና በህብረት ብቻ ሳይሆን በግላችን፣ በአእምሮአችን፣ በሰውነታችን፣ በስሜታችንና በማንነታችን ሁሉ ነው። ፈርጀ ብዙ በሆነው በግል ኑሮአችን እንዲሁም በቤተሰባችን እና በግንኙነቶቻችን ሁሉ መካከል እርሱን ማክበርና ደስ የሚያሰኘውን ለማድረግ መትጋት እንዳለብን እንዲህ ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል ያዝዘናልም፤      

 “ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኩስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ።” ሮሜ 6፡19 ይለናል

  ስለዚህ መነፈሳዊ ቤት ሆነን ለመሰራት ከርኩሰትና ከዓመጻ ልንለይ ያስፈልጋል ማለት ነው

 

 

“እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ”

ክፍል 2.

“እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፣እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፣ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲህ አድርጉ፣ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ። የምታመሰግኑም ሁኑ፣ የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፣ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገስፁ፣ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፣ እግዚአብሔርን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።”  (ቆላስይስ 3፡12-17)

 

   ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ስንቀበል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእግዚአብሔር ዳግም ተወልደናል፣ ስለዚህ አዲስ ፍጥረቶች ነን። ኃጢዓት ካመጣብን የዘለዓለም ሞት ድነናል፣ ስለዚህም በክርስቶስ ጽድቅ ምክንያት ጻድቃን ሆነናል። በዓመጻችን ምክንያት ተጣልተነውና ተለይተነው ከነበረው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ ደም ታርቀናል፣ ስለዚህም የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይገዛን ከነበረውና ዛሬም የማያምነውን ዓለም ከሚገዛው ከጨለማው ገዥ ከዲያብሎስ፣ ከጭፍሮቹና ከአጋንንት ስልጣን ነጻ ወጥተን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር መንግሥት ፈልሰናል፣ በጨለማው ገዥና  በሥርዓቱም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጥቶናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲገለጽ እኛም ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር እንድንገለጥና አብረነው በሕይወት እንድንነግስ ታጭተናል። እነዚህን እውነቶች ሁሉ እንዳንረሳ፣ እንዳንደክምና እንዳንታክት፣ ወደ እውነት ሁሉ እንዲመራንና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገልንን እና ያስተማረንን የሚያስታውሰንን መንፈስ ቅዱስን እንደ ርስታችን መያዣ ተቀብለናል

(ዮሐ 1፡12-13 ዮሐንስ 3፡16-18 ሮሜ 5፡1-2 ሮሜ 6፡6 2ኛ ቆሮ 5፡17 ቆላስይስ 1፡13-14 ሉቃስ 10፡19-20)

በዚህ ሁሉ እውነት ለተከበብን ክርስቲያኖች ነው ታዲያ ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ” የሚለን። ልጆች በብዙ መንገድ ወላጆቻቸውን እንደሚመስሉ ሁሉ እኛም በክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዳግም የተወለድን ክርስቲያኖች ዳግም የወለደንን እግዚአብሔርን እንድንመስል ይጠበቅብናል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎአል፡

“እናንተ ስለነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፣ በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና፣ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፣እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ....ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።” ዮሐንስ ወንጌል 15፡3-8

  ስለዚህ መንፈሳዊ ቤት ለመሆንና ለመሰራት ከግንዱ ከኢየሱስ ጋር እንጣበቅ አሜን !!!!

 

ክፍል 3  

እናንተ የእፉኝት ልጆች !

“እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?”  ማቲ 3፣7 ( የ1954 ትርጉም )

ዮሃንስ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደሚያጠምቅበት ስፍራ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ ''እናንት የእፉኝት ልጆች! ..... ለንስሃ የሚገባን ፍሬ አፍሩ''  በመሃል ያለውን እናንተ እንድታነቡት ትቼዋለሁ።  ዮሃንስ በዚያን ጊዜ ወደሱ ከመጡት ውስጥ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው አይሰማቸውም ነበር። እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ይጠመቁ የነበሩትን ሊሎችን ሰዎች ይንቋቸው ነበር። ዮሐንስ፣ እነዚህን ግብዝ መሪዎች እንዲህ ጠርቷቸው ነበር :- “እናንተ የእፉኝት ልጆች''........ ለምን እንዲህ ጠራቸው ? እስኪ እፉኝት ማናት?

እፉኝት እንደማንኛውም እንሰሳ ስትሆን፣ የእድሜ ጣሪያዋ አርግዛ እስከምትወልድ ብቻ የተገደበ ነው። የባሏም እድሜ ከሷ ግንኙነት(ሩካቤ) እስኪያደርግ ብቻ ነው። የመጀመሪያ ሩካቤ ካደረጉ በኋላ የባሏን ብልት ትበላና ትገድለዋለች። የምታረግዘውም በአንድ ጊዜ ግንኙነት ብቻ ስለሆነ ታረግዝና መውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ ልጆቿ የሚወለዱት እንደ ብዙዎች እንሰሳት በመወለጃ ብልቷ ሳይሆን ሆድዋን በልተው በመቅደድ ስለሆነ እሷም እንደ ባሏ ትሞትና የወለደቻቸው ልጆች ያለ እናትም ያለ አባትም ይድጋሉ ይህ ሂደት እንግዲህ ለእፉኝት ቀጣይ የህይወት ሂደት ነው ማለት ነው። ታዲያ ዮሃንስ ለምን እነዚህን ሰዎች የእፉኝት ልጆች አላቸው ? አይገርምም እፉኝቶች እየተገዳደሉ ሂደት እንዲቀጥል ያደርጋሉ።

ስለዚህ የዛሬውን መልእክቴን ይህን ጥያቄ ጠይቄያችሁ ልለፍ ዛሬ ዮሃንስ ቢኖር እኛን ምን ብሎ ይጠራን ይሆን ??

ስለዚህ መንፈሳዊ ቤት ሆነን ለመሰራት እርስ በርስ ከመነካከስና ከመበላላት ከመጠፋፋትም እራሳችንን እንጠብቅ እንጠንቀቅም ቃሉ እንደሚለን

'' ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ'' ይለናል ። ገላ 5፣15 አሜን !!!

 

ክፍል 4

 “   ......  ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?”  ማቲ 3፣7

 

  ዮሃንስ ከፈሪሳዊያንና ከሰዱቃዊያን ብዙዎች ወደ እርሱ ሲመጡ ሲያይ እነዚህ አብርሃም አባት አለን እያሉ የሚመጻደቁ በሰዎች ንስሃ መግባት የሚያሾፉ በራሳቸው ላይ ጥፋትን እየከመሩ ያሉ የሃይማኖት ሰዎችን ያለፍርሃት እያስጠነቀቀ ያሳስባቸው ነበር። ዮሃንስ እነዚህን ሰዎች እያባረረ እያሳደደ ከበስተኃላቸው የሚከተላቸው ቁጣ የተባለ ነገር እንዳለ በመንፈስ ተረድቶ ሲናገራቸው እናያለን ። ዮሃንስ እየመጣ ያለ ቁጣ አለ ይህ ቁጣ ደግሞ የሚምር አይደለም የሚያጠፋ እንደደራሽ ውሃ ትልቅ ሃይል ያለው ነው ፣ ይህ እንደ ደራሽ ውሃ እየመጣ ያለው ቁጣ ደግሞ የተቀመጠውንም፣የተኛውንም፣ ስር ሰዶ የተተከለውንም፣ በተለያየ መሰረት የተገነባውንም ሁሉ ገንድሶ የመጣል፣ የማፈራረስና የመበታተን ሃይል ያለው ነው ። ከዚህ ኃያል ቁጣ እንድታመልጡና እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ ማን መከራችሁ እያላቸው ነበር።

   ዛሬም እየመጣ ያለ የእግዚአብሄር ታላቅ የክብር ደምና አለ በዚህ በክብር ደመና ውስጥ ደግሞ የሚያጠራ እሳት አለ። ይህ እሳት የእግዚአብሄር ክብር የሚያርፍበትን ስፍራ የተስተካከለ እንዲሆን የሚያጠራና የሚያስተካክል እሳት ነው ። ይህ እሳት በውስጥም በውጭም ያለውን ከክብሩ ጋር ሊሄድ የማይችለውን ሁሉ ያቃጥላል (ልክ ወርቅ በእሳት እንደሚጠራ) ይህ ታላቅ ቁጣ እንዳይመጣብን እንጠንቀቅ። የእግዚአብሂር የክብሩ ማደሪያ ቤት ሆኖ ለመሰራት ልክ ቤት ሲሰራ ድንጋዩም ብረቱም በእሳት ግሎ በመዶሻ ተቀትቅጦ ተጠርቦ መልክና ውበት እንደሚያወጣ ሁሉ የእኛም ሁለንተናችን ማለትም መንፈሳችን፣ ነፍሳችን፣ ስጋችን የተመቸ እንዲሆን በየእለቱ በመንፈስ ቅዱስ እሳት ሊቃኝና ሊሞላ ያስፈልገዋል። ከወይን ጠጅ ይልቅ በየዕለቱ ልንሞላበት የሚገባን፣ ኢየሱስ እኔ ብሄድና እሱ ቢመጣላችሁ ይሻላችኃል ያለለት ቅዱስ የሆነ መንፈስ አለንና ።

   ስለዚህ ወገኖቼ ዛሬ የእግዚአብሄር የክብሩ ማደሪያ ቤት ሆነን ለመሰራት ራሱ የሰላም አምላክ (መንፈሳችንን ፣ ነፍሳችንን ፣ ስጋችንን ) ጌታ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ያለነቀፋ ሆነን እንድንጠብቀው  ሁለንተናችንን ይቀድስ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፣23 ) አሜን !!!

ክፍል  5

ልንሸሻቸው የሚገቡ ነገሮች !

 

“እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?” —ማቴ. 3:7 የ1954 ትርጉም

ከመሸሽ ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስብዙ የሚለው ነገር አለ።

‘ሽሹ’ የሚለውን ቃል ስንሰማ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ምንድን ነው? አንዳንዶቻችን ዮሴፍ የተባለው መልከ መልካም ወጣት፣ የጲጢፋራ ሚስት ከእሷ ጋር እንዲተኛ በጠየቀችው ጊዜ መሸሹን እናስታውስ ይሆናል። አንዳንዶቻችን ከኢየሩሳሌም የሸሹትን ክርስቲያኖች እናስብ ይሆናል፤ አንዳንዶቻችን ከዝሙት ሽሹ እንዲሁም ከጣዖት ሽሹ የሚሉ ሃሳቦች በዓእምሮአችን ያቃጭልብን ይሆናል።

 

ካላይ ያየናቸው ሰዎች በዓካልና በሃሳብ መሸሽ ካለባቸው ነገር ሲሸሹ የሚያሳይ ነው በዛሬው ጊዜም በዓለም ዙሪያ የምንኖር እውነተኛ ክርስቲያኖች  በአስቸኳይ መሸሽ ያለብን ነገሮች አሉ። መጥምቁ ዮሐንስ ‘መሸሽ’ የሚለውን ቃል የተጠቀመበት በዚህ መንገድ ነበር። ዛሬም እኛ ልንሸሻቸው የሚገቡ ጌታ የማይፈልጋቸው አብረናቸው እየኖርን ያለነው ብዙ የተጣበቁብን ተጋብተናቸው አብረን እየኖርን ያለነው የህይወት ዘይቤዎች እንደሎጥ ተቀላቅለን እየኖርንባቸው ያለንበት አካባቢዎች አሉ ከዚህ ህይወት መላቀቅና መሸሽ አለብን። መንፈሳዊ ቤት ሆነን ለመሰራትና ጌታ እንዲኖርብን ካስፈለገ አንዱ መንገድ ከገባንበት ጌታ ከማይከብርበት የህይወት ኑሮ ሎጥ ሰዶምን ጥሎ  እንደታዘዘና እንደወጣ ዮሴፍ ከጴጢፋራ ሚስት እንደሸሸ እኛም በአስቸኳይ ልንወጣ ያስፈልጋል። ዛሬም እንደሎጥ አስቸኩሎ የሚያወጣ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል አለና እራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ እናስረክብ በሃሳብም በዓካልም እጃችንን ይዞ ያወጣናል።

መንፈስ ድካማችንን ያግዛልና ። አሜን !!!

 ካሱ ቦስተን

የልጁን መልክ እንዲመስሉ !

መጽሃፍ ቅዱስ በሮሜ 8፤29 ላይ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና ይላል።

   

ኤፌሶን 1:5 በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።

ኤፌሶን 2 :10 እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።

 

    እግዚአብሄር አምላክ አለምን ከመፍጠሩ በፊት የእኔንና የእናንተን ፍጻሜ አዘጋጅቶ ወስኖ አስቀምጧል። የእኛ ስራ መሆን ያለበት ይህንን የእግዚአብሄርን ሃሳብ አውቀን መራመድና መጓዝ ነው።

    ወንድሞችና እህቶች አካሄዳችን ወዴት ነው? የኑሮአችን አላማ ምንድነው? በምድር ላይ ስንኖር በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም የተወለድንበት ወይም እግዚአብሄር አምላካችን ዳግም የወለደን ለምንድነው? ዛሬ ላይ ሆነን አካሄዳችንን ቆም ብለን እየሄድን ያለነውን  ጉዞ ማጤን አለብን ። የተሳፈርንበት የጉዞ ባቡር ወይም አውቶቡስ በትክክል ወደፍጻሜያችን የሚያደርሰን ነወይ? ወይስ በየመንገዱ በየፌርማታው የሚያንጠባጥበን ? ጉዟችንን ከመጀመራችን በፊት ወዴት እንደምንሄድ በየትኛው ትራንስፖርት መሄድ እንዳለብን ካላወቅን ጉዞአችን በጣም አደገኛና ወደማንፈልገው አቅጣጫ እንደሚወስደን ልንረዳና መጨረሻው መጥፋትና ከአካባቢ መራቅ እንደሚያስከትል ልንገነዘበው ይገባል።

    ወገኖቼ እግዚአብሄር አስቀድሞ የእኛን ጉዞ ወይም የእኛን ፍጻሜ አንድያና የበኩር ልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ እንመስል ዘንድ ነው እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ልጁን መቅረጽና ማየት ይፈልጋል። እንግዲህ መንፈሳዊ ቤት ሆነን ስንሰራ የቤቱ ፍጻሜና መልኩ መሆን ያለበት ልክ ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ነው ማለት ነው።  አሜን  !!!

አቅጣጫችን  ወዴት ነው ??

 

"ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።" (ዮሐ.3፡8)

 

   አንድ ገበሬ እርፉን ለሚጎትተው የበሬዎች ኃይል መገዛትና እርፉን ጨብጦ እነርሱ ወደሚሄዱበት አቅጣጫ ብቻ መሄድ እንደሚገባው ሁሉ አንድ ደቀ መዝሙርም የእግዚአብሔርን መንግስት ማለትም ክርስቶስን ካገኘ በኋላ ለመንግስቱ ጉልበት ተሸንፎ መንግስቱ ወደምትሄድበት አቅጣጫ ብቻ የሚሄድ ነው። ከእግዚአብሔር የተወለደ የመንግስቱ ደቀመዝሙር በነፋስ መመሰሉና ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አለመታወቁ ለምን ይሆን? በራሱ መንገድና መርህ «እናቴንና አባቴን ልቅበር ልሰናበት» በሚለው መርህ መመላለስ አቁሞ በመንግስተ ሰማያት ምህዋር ውስጥ ስለገባ አይደለምን? እናቱንና አባቱን ሊቀብርና ሊሰናበት የሚሄደውንማ ሁሉም ሰው ከየት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ ያውቀዋል የሰው ሁሉ ምልልስ ነውና። ከእግዚአብሔር ተወልደን የክርስቶስን ማንነት ተካፍለን «ከመንፈስ የተወለደ» ስንሆን ግን እንቅስቃሴአችን ሁሉ በእግዛኢብሔር መንፈስ የሚመራ፣ በጉ ወደሚሄድበት ብቻ የሆነ ለሰዎች የማይታይና በሰዎች የማይገመት ይሆናል። ዓለም የሰው ልጆች እንዲመላለሱበት በቀረጸችው የኑሮ መርህ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንግስት ስርዓት እንመላለሳለን። የሂደታችን አቅጣጫ ሰዎች ወደሚሄዱበት አይደለም በጉ ወደሚሄድበት እንጂ። እንደ ነፋስ በዚህ ዓለም እንዳለን ይታወቃል፣ ሰዎች ድምጻችንን ይሰማሉ፣ የእንቅስቃሴአችንን ዱካ ግን ሊያውቁ አይችሉም። እንቅስቃሴአችን በጣም ዝቅተኛ ከሆነው የሰው ልጆች መርህ ወጥቶ በመንግስቱ መንኮራኩር ውስጥ ተሰውሮአልና። የእንቅስቃሴአችን እዝ ማእከል እግዚአብሔር እንጂ ስጋና ደም፣ የምድር ሥርዓት፣ ፖለቲካ፣ ምድራዊ ጥበብ በጭራሽ አይደለም። ወደ መንግስቱ ስንመጣ የመንግስቱ ጉልበት ዑደት (አዙሪት) ወደርሱ ጎትቶ ካላስገባንና ለዚህ ሰማያዊ ጉልበት ወዲያው ተሸንፈን ኢየሱስን ካልተከተልን የመንግስተ ሰማይ ደቀመዝሙር አይደለንም።

  ደቀመዝሙርነት ተለምኖ የሚኮን ነገር ሳይሆን ምንም ኃይልና ብቃት እስከማይቀርልን ድረስ በመንግስቱ ጉልበት ተዘርረን ራሳችንን የምናገኝበት ህይወት ነው። "ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል።" መባሉስ ለዚህ አይደል? ለመሆኑ እነዚህ ግፈኞች በማን ላይ ነው ግፍ የሰሩት??? በራሳቸው ላይ ነዋ። መንግስተ ሰማያት ከዮሐንስ ጊዜ ጀምሮ በሃይማኖት መሪዎች ሁሉ ተገፍታለች ሰዎች እንዳይቀበሏት እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በአመጽ ገፍተዋታል። እንግዲህ ወደርስዋ መግባትን የሚሹ ሁሉ ፈሪሳውያን መንግስቱን ላለመቀበል ካመጹበት በሚበልጥ ሁኔታ ለፈሪሳውያን ስርዓትና ለራሳቸው ህይወት ሳይራሩ በማመጽ ወደ እርስዋ በኃይል ለመግባት የነበሩበትን ስርዓትና ሃይማኖት የገፉ ግፈኞች መሆን አለባቸው። ስለዚህ «መንግስተ ሰማያት ትገፋለች» ሲል ፈርሳውያን ለስርዓታቸው ብለው የእግዚአብሔርን መንግስት እንደገፏት ለመግለጥ ሲሆን «ግፈኞች ይናጠቋታል» ሲል ደግሞ የፈሪሳውያኑን መንግስተ ሰማያትን የሚገፋውን ግፍ ገፍተው በኃይል ወደርስዋ የመጡትን ማለቱ ነው።

ካሱ ቦስተን   

bottom of page